በጋዛ የተኩስ አቁም ለማምጣት ዶሃ ላይ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የሁለት ቀናት ንግግር መጠቃለሉንና በመጪው ሳምንት ካይሮ ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ እንዳቀዱ አደራዳሪዎቹ አስታውቀዋል።
አደራዳሪዎቹ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ግብጽ እና ቃጣር ዛሬ ባወጡት መግለጫ፣ ንግግሩ ገንቢ እንደነበርና በጥሩ መንፈስ የተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። ለሁለቱም ወገኖች ያላቸውን ሃሳብ ማቅረባቸውንና፣ በሚቀጥሉት ቀናትም መሥራት እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
SEE ALSO: በጋዛ ተኩስ ማቆም እንዲደረግ በዶሃ ጥረቱ ቀጥሏልከትላንት ሐሙስ ጀምሮ የተደረገው ንግግር ለ10 ወራት የቆየውን ጦርነት ለማስቆምና ታጋቾችን ለማስለቀቅ ያለመ ነበር። በስምምነት የሚቋጭ ከሆነ ደግሞ በቀጠናው ሊስፋፋ ያለውን ጦርነት ለመቀልበስ ያስችላል ተብሏል።
ሁለቱም ወገኖች በመርህ ደረጃ ፕሬዝደንት ባይደን ባቀረቡት ሃሳብ ላይ የተስማሙ ሲሆን፣ ሃማስ ማሻሻያ በማቀረቡ፣ እስራኤል ደግሞ ማብራሪያ በመጠየቋ አንዱ ሌላውን በአደናቃፊነት በመክሰስ ላይ ነው።
በውይይቱ ላይ በቀጥታ ያልተሳተፈው ሐማስ፣ አዲስ ጥያቄዎችን ታቀርባለች ሲል እስራኤልን ከሷል።
አደራዳሪዎቹ ክፍተቶችን የደፈነ ነው ያሉትን ሃሳብ ለሁለቱም ወገኖች ማቅረባቸው አስታውቀዋል።
አዲሱ ተስፋ የመጣው፣ በጋዛ የሟቾች ቁጥር ከ40 ሺሕ መዝለሉ በሚነገርበትና፣ ኢራን እና ሄዝቦላ እስራኤልን ለመበቀል ጥቃት ይሰንዝራሉ በሚባልበት ወቅት ነው።