ታጋቾች እስከሚለቀቁ ከበባው ይቀጥላል - እስራኤል
በጋዛ ሰርጥ የምድር ውጊያ ለመጀመር ዝግጅት ላይ መሆኗን እስራኤል ዛሬ ሐሙስ አስታውቃለች፡፡ ዘመቻውን በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ገና እንዳልተደረሰ ተነግሯል።
በሐማስ ጥቃት 1ሺሕ 200 ሰዎች የተገደሉባት እስራኤል፣ 300ሺሕ ተጠባባቂ ጦሯን ጠርታ በድንበር ላይ አከማችታለች፡፡እስራኤል በምላሹ በወሰደችው የአጸፋ ጥቃት በጋዛ 1ሺሕ 350 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በጋዛ 340 ሺሕ ሰዎች ከቤታቸው ሲፈናቀሉ፣ ከእነዚህ ውስጥ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት በተመድ በሚተዳደሩ ትምሕርት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ ሲል ድርጅቱ አስታውቋል።
እስራኤል ጋዛን ከበባ ውስጥ በማዋሏ፤ የምግብ፣ የውሃ፣ የነዳጅ እና የመድሃኒት አቅርቦት ሁኔታው የረዴት ድርጅቶችን አስጨንቋል።
ሐማስ ታጋቾችን እስኪለቅ ድረስ ከበባው እንደሚቀጥል የእስራኤሉ የኃይል ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ተናግረዋል።