የፍልስጤም ባለሥልጣናት በጋዛ 30 ሰዎች በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን ተናገሩ

  • ቪኦኤ ዜና

ወጣቱ በእስራኤላውያን ጥቃት ከፈረሰው የሕንፃ ፍርስራሹን እቃዎች እየወሰደ እአአ ኅዳር 5/2024

እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው የአየር ድብደባ በትንሹ 30 ሰዎች ሞተዋል ሲሉ የፍልስጤም የጤና ባለስልጣናት ዛሬ ማክሰኞ አስታወቁ፡፡

ትላንት ሰኞ ምሽቱን በቤቴላሂያ ብቻ በተካሄደ ጥቃት በትንሹ 20 የሚደርሱ ተፈናቃይ ቤተሰቦች መገደላቸውን ባለስልጣናቱ ገልጸዋል፡፡

በማዕከላዊ እና በደቡባዊ በጋዛ ዙዋይዳ እና ዴይር አል ባላህ ተጨማሪ የአየር ድብደባዎች መፈጸማቸውም ተመልክቷል፡፡

የእስራኤል ኃይሎች ታጣቂዎችን መግደላቸውን እና መሠረተ ልማቶቻቸውን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን ማካሄዳቸውን የእስራኤል ጦር ትላንት ማክሰኞ አስታውቋል፡፡

ሊባኖስ ውስጥ በእስራኤል እና በሂዝቦላ መካከል 13 ወራት በዘለቀው ግጭት ከ3,000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እና ከ13ሺ በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል፡፡ ከሚሊዮን በላይ የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡

አብዛኞቹ የሞቱት ግጭቱ እያየለ ከመጣበት እና እኤአ ህዳር 1 እስራኤል ደቡብ ሊባኖስን ከወረረች ወዲህ ነው፡፡ ከሞቱት መካከል ሲቪሎች እና ፣ እንደ ሀሰን ናስራላህ ያሉ የሂዝቦላህ መሪዎችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቡድኑ አባላት ይገኙበታል፡፡

በእስራኤል በኩል 30 ወታደሮችን ጨምሮ ፣72 ሰዎች ፣ በሂዝቦላህ ሮኬት እና በድሮን ጥቃቶች ሞተዋል፡፡

የሊባኖስ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ ጦርነቱን ለማስቆም ፣ ሲቪሎችን ለመጠበቅ እና እንደ ጢሮስ እና ባአልቤክ ያሉ ታሪካዊ ቦታዎችን ከእስራኤል የአየር ድብደባ ለመጠበቅ አስቸኳይ ዓለም አቀፍ ጣልቃገብነት እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል ።