እስራኤል ተጠባባቂ ብርጌድ ክፍለ ጦሮች ወደ ጋዛ ሰርጥ ላከች

  • ቪኦኤ ዜና
ፎቶ ፋይል፦ ምየእስራኤል ወታደሮች ጋዛ ሰርጥ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ያሳያል፤ እአአ ሚያዚያ 22/2024

ፎቶ ፋይል፦ ምየእስራኤል ወታደሮች ጋዛ ሰርጥ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ያሳያል፤ እአአ ሚያዚያ 22/2024

"ሁለት ተጠባባቂ ብርጌዶችን ወደ ጋዛ ሰርጥ አዝምተናል" ሲል የእስራኤል ጦር ኅይል ዛሬ አስታወቀ። ተጠባባቂ ብርጌድ ክፍለ ጦሮቹ የተላኩት እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ በምድር ጦር ጥቃት ለመክፈት እየተዘጋጀች ባለችበት በዚህ ወቅት ነው።

የእስራኤል የጦር ኃይል ዝርዝር ውስጥ ሳይገባ “ የተላከው ሠራዊት የመከላከል እና የታክቲክ ተልዕኮዎችን ያከናውናል” ብሏል፡፡ የእስራኤል ባለሥልጣናት “የሃማስን ታጣቂዎች የመደምሰስ ግባችንን ለማሳካት ራፋህ ላይ ጥቃት መክፈት በግድ ያስፈልገናል” ሲሉ ቆይተዋል፡፡

ሁለት ተጠባባቂ ብርጌዶችን ወደ ጋዛ ሰርጥ አዝምተናል"

ዩናይትድ ስቴትስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎችም ከባድ ሰብአዊ ቀውስ ያስከትላል በማለት እስራኤል ራፋህ ላይ በየብስ ልትከፍት ስላቀደችው ጥቃት ስጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። በሌሎች የጋዛ አካባቢዎች ከሚኖሩ ሰዎች ውስጥ ከግማሽ የሚበልጡት ራፋህ ላይ ተጠልለዋል፡፡ ብዙዎቹ ውጊያውን በመሸሽ እስራኤል በሰጠችው ትዕዛዝ መሰረት ቀያቸውን ለቀው የወጡ ናቸው፡፡

ዛሬ ረቡዕ የእስራኤል የጦር ኃይል በሰጠው መግለጫ ተዋጊ ጄቶቹ ትናንት ጋዛ ውስጥ ያሉ ከሃምሳ የሚበልጡ ዒላማዎቹን መደብደባቸውን ገልጿል፡፡ እስራኤል ደቡባዊ ሊባኖስ ያሉ የሄዝቦላህ ይዞታዎች ላይም ጥቃት ማድረሷን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል። ጥቃቱ ታጣቂው ቡድን “ቀደም ብሎ እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት ሲቪሎች መግደሏን ለመበቀል ነው” በሚል ላደረሰው የሮኬት ጥቃት አጸፋም ጭምር መሆኑን እስራኤል አስታውቃለች፡፡

ሃማስ እና ሄዝቦላህ በዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪነት የተፈረጁ ቡድኖች ናቸው፡፡