ጋዛ ከተማ ውስጥ በሚገኘው አል ሺፋ ሆስፒታል አካባቢ እና በደቡባዊ ጋዛ ካን ዩኒስ መንደር ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን የእስራኤል የጦር ኃይል አስታወቀ።
ሃማስ የሚያስተዳድረው የጋዛ ሰርጥ የጤና ሚንስቴር በበኩሉ ትናንት ረቡዕ 62 ፍልስጥኤማውያን መገደላቸውን ዛሬ አስታውቋል፡፡
ሃማስ በጥቅምት ወር ባደረሰው ጥቃት 1200 ሰዎች መግደሉን ተከትሎ እስራኤል በከፈተችው የአጸፋ ጥቃት ቢያንስ 32 ሺህ 552 ሰዎች መገደላቸውን የጤና ሚንስቴሩ አክሎ አስታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል የቀደመውን አቋሟን ቀልብሳ ደቡባዊ ጋዛ ራፋ ከተማ ላይ ልትከፍት ስላሰበቸው የየብስ ጥቃት ለመነጋገር የጦርነት ስትራተጂ አውጪዎቿን ወደ ዋሽንግተን ለመላክ ተስማምታለች፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም የተመድ የጸጥታ ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣኗ ተጠቅማ ውድቅ ባለማድረጓ እስራኤል ተቃውሞዋን ለመግለጽ የመልዕክተኞቹን ጉዞ ሰኞ ዕለት ሰርዛው ነበር፡፡
መንፈቅ ሊያስቆጥር በተቃረበው የጋዛው ጦርነት የእስራኤል ጠንካራ ደጋፊ የሆነችው ዩናይትድ ስቴትስ በጸጥታው ምክር ቤት ከዚህ ቀደም የቀረቡ ተመሳሳይ ውሳኔዎችን ድምጽን በድምጽ በመሻር ስልጣኗ እንዳያልፉ ማድረጓ ሲታወስ በዚህ ሳምንት በቀረበው ውሳኔ ድምጽ ተአቅቦ አድርጋለች፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የአሜሪካንን ውሳኔ ያወገዙ ሲሆን፣ አገራቸው ከጦርነቱ አካሄድ ጋራ በተያያዘ ከዋሽንግተን ጋር ያላት ልዩነት እየሰፋ መሆኑን የሚያመለክት ተደርጎ ተወስዷል፡፡
ኔታንያሁ የጦርነት ዕቅድ አውጪዎቹን ጉዞ በሰረዙበትም ጊዜ የመከላከያ ሚንስትሩ ዮአቭ ጋላንት ከዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስተን እና ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንከን ለመነጋገር በዚህ ሳምንት ዋሽንግተንን ጎብኝተዋል፡፡
ኔታንያሁ በእስራኤል ጉብኝት ካደረጉት ከዩናይትድ ስቴትስ ሪፐብሊካን ሴኔተር ሪክ ስካት ጋር በነበራቸው ውይይት፣ ዩናይትድ ስቴትስ ድምጸ ተዐቅቦ ማድረጓን “መጥፎ” ውሳኔ ሲሉ ገልጸው፣ “የልዑካኑ ጉዞ ስረዛችን በዋናነት ያነጣጠረው ሀማስ ላይ ነው” ብለዋል፡፡
“የተባበሩት መንግሥታት በሚያደርገው ጫና ላይ አትተማመኑ አይሰራም የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ፈልገን ነው” ሲሉ አክለዋል፡፡ ከእስራኤል ባለሥልጣናት ጋር ውይይት መቀጠሉ መልካም እንደሆነ የገለጸው ኋይት ሀውስ ፣ ቀጣይ ውይይቱ መቼ እንደሚሆን በመነጋገር ላይ ነን ሲል አስታውቋል፡፡