እስራኤል ዛሬ ረቡዕ በጋዛ ሰርጥ ላይ አዲስ የአየር ድብደባ ስትፈጽም የሀገሪቱ ጦርም በቤይሩት የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣንን የገደለበትን የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቱን ተከትሎ በሊባኖስ ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላህ ለሚሰነዘረው ጥቃት በተጠንቀቅ ላይ ነኝ ብሏል፡፡
ሐማስ እና የአካባቢው የጸጥታ ባለሥልጣናት ሳሌህ አል አሩሪን የገደለው ጥቃት የእስራኤሉ ሰው አልባ አውሮፕላን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በኢራን የሚደገፈው ሂዝቦላህ ልክ እንደ ሐማስ፣ በዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪነት የተፈረጀ ታጣቂ ቡድን ሲሆን የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጥቅምት ወር ጀምሮ በእስራኤል ሰሜናዊ ድንበር ላይ ሮኬቶችን ሲተኮስ ቆይቷል።
አሩሪ በሐማስ ፖሊት ቢሮ ውስጥ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩ ሲሆን ከወታደራዊ ክንፉ አንዱ የሆነውና
በእስራኤል ግዛት ውስጥ ዘልቆ በመግባት እኤአ ጥቅምት 7 የተፈጸመውን አስከፊውና አስደንጋጭ ጥቃት የፈጸመው የከሳም ብርጌድ መስራቾች አንዱ ናቸው፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ ባለፈው ዓመት ስለ አሩሪ መረጃ ለሚሰጥ 5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እንደምትስጥ አስታውቃ ነበር፡፡
የእስራኤል ጦር ስለ አሩሪ ሞት አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ጥቃት ሦስት ወር ሊሞላው በተቃረበው የጋዛው ጦርነት እየሩሳሌም ቁልፍ የሐማስ መሪዎችን ለመግደል ከገባችው ቃል ጋር የሚስማማ ነው ተብሏል፡፡
ስለ አሩሪ ግድያ የተጠየቁት የእስራኤል ወታደራዊ ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ "ዛሬ ማታ መናገር ያለብን በጣም አስፈላጊው ነገር ትኩረታችን ሐማስን በመዋጋት ላይ መሆናችን ነው" ብለዋል።
የሊባኖስ መንግሥት የዜና ወኪል እንደዘገበው በሊባኖስ ዋና ከተማ ደቡባዊ ዳርቻ በተጨናነቀው መንደር ውስጥ በሐማስ ፅህፈት ቤቶች ላይ በደረሰ ጥቃት አራት ሰዎች ተገድለዋል።
ሂዝቦላህ በመግለጫው “ይህ ወንጀል መልስ ሳይሰጠው ወይም ቅጣቱን ሳያገኝ አይቀርም” ሲል “በጦርነቱ ሂደት ውስጥ የታየ አደገኛ ክስተት ነው” ብሏል።
እስራኤል ሂዝቦላ ከድርጊቱ ካልተቆጠበና ካላረፈ ሊባኖስ ላይ ሙሉ በሙሉ ጦርነት ሊነሳ እንደሚችል አስጠንቅቃለች። ሃማስም ሆነ ሂዝቦላ በኢራን የሚደገፉ ሲሆኑ በሶሪያ፣ ኢራቅ እና የመን የሚገኙ ታጣቂ አጋሮቻቸው በእስራኤል ላይ የረዥም ርቀት ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል።