ዛሬ የእስራኤል የጦር ኃይል ባወጣው መግለጫ ከኋለኛው የአየር ድብደባው ዒላማዎች ውስጥ ሃማስ የሚጠቀምባቸው ግቢዎች እንደሚገኙበት አመልክቷል፡፡ ወታደሮቹ ደቡብ ጋዛ የሚገኝ መሿለኪያ መደምሰሳቸውን መግለጫው አክሏል፡፡
ከግብጽ ጋር በምትዋሰነው እና ውጊያውን ሽሽተው የተሰደዱ ብዙ ሺህ ሲቪሎች በሚገኙባት በደቡብ ጋዛ ራፋ ከተማ ውስጥ በእስራኤል የአየር ጥቃት ቢያንስ 20 ሰዎች መገደላቸውን በሃማስ ስር ያለው የጋዛ የጤና ሚንስቴር አስታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት ለፍልስጥዒማውያን ሲቪሎች አስፈላጊ ሰብዓዊ እርዳታ ሲባል ውጊያው እንዲገታ በሚጠይቀው ውሳኔ ላይ ዛሬ ድምጽ ይሰጣል፡፡
የውሳኔው ደጋፊዎች በቂ ድምጽ አግኝቶ ለማለፍ የሚያስችለው ድጋፍ ለማሰባሰብ ጥረት እያደረጉ ሲሆን በውሳኔው ሰነድ ዙሪያ ድርድሩ በመቀጠሉ ለትናንት ታቅዶ የነበረው የድምጽ አሰጣጥ ወደዛሬ ተላልፏል፡፡
ለሰብዓዊ እርዳታ ሲባል ተኩስ እንዲቆም በመጠየቅ ባለፈው ወር በጸጥታ ምክር ቤቱ የቀረበውን ውሳኔ ዩናይትድ ስትቴስ ውሳኔ በመሻር ስልጣኗ ተጠቅማ እንደጣለችው ይታወሳል፡፡ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ባለፈው ሳምንት ተመሳሳይ ነገር ግን አሳሪ ያልሆነ ውሳኔ በከፍተኛ ድምጽ አሳልፏል፡፡