የእስራኤል ወታደሮች ዛሬ ማክሰኞ በደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ በፈጸሙት የአየር ድብደባ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን የፍልስጤም የጤና ባለስልጣናት ተናገሩ። እስራኤል ፍልስጤማውያን ሲቪሎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ካዘዘች አንድ ቀን በኋላ ያካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ በካን ዩኒስ የፈጸመቸውን የአየር ድብደባም ይጨምራል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ በዛሬው ዕለት ይፋ እንዳደረገው፣ ታጣቂዎች እስራኤላውያን ሰፋሪዎች ወደሚገኙባቸው መንደሮች የተኮሷቸውን ከ20 በላይ ሮኬቶች ‘ለማስወንጨፍ ተጠቅመውባታል’ ያላትን ካን ዩኒስን ለሊቱን በአየር ደብድቧል። ሌላው የእስራኤል የአየር ድብደባ በደቡባዊቱ የራፋህ ከተማ ላይ የተነጣጠረ ሲሆን፤ የእስራኤል እግረኛ ጦርም ማዕከላዊ ጋዛ ውስጥ በሃማስ ላይ ጥቃት ማድረሱን የገለጸበትን ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄዱ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች ትላንት ሰኞ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት፤ እስራኤል ፍልስጤማውያን ካን ዩኒስን ለቀው እንዲወጡ የሰጠችው ትእዛዝ “ጋዛ ውስጥ ለሲቪሎች ደህንነት የሚመረጥ ምንም አይነት ሥፍራ ያለመኖሩን እና የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥረት መደረግ እንዳለበት የሚያሳይ ነው” ብለዋል።
እስራኤል በአየር ድብብደባው እና ሌሎች ወታደራዊ እርምጃዎች ሊደርሱባቸው ከሚችሉ አደጋዎች ፍልስጤማውያኑን ለመታደግ የታለመ መሆኑን ባመለከተችው ትዕዛዝ ጥቃቱን ከመፈጸሟ አስቀድማ ሰላማዊ ሰዎች የተወሰኑ የጋዛ አካባቢዎችን ለቀው እንዲወጡ ደጋግማ አስጠንቅቃለች። ይሁንና እርምጃው ፍልስጤማውያኑ ባለፉት በርካታ ወራት ከመሰል ጥቃቶች በመሸሽ በተደጋጋሚ ለመሰደድ እንደተዳረጉት ሁሉ አሁንም ዳግም ለሌላ ስደት የሚዳርጋቸው መሆኑ ታምኗል።
"የጋዛ ሕዝብ ባልተቋረጠ አውዳሚ አዙሪት ውስጥ እንዲያልፍ የሚያስገድድ ሌላ ድንገት ነው" ያሉት የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ይህንኑ አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት "ለግጭቱ ማብቂያ ሁነኛ ማበጀት ያለብን ለዚህ ነው" ብለዋል።
እስራኤል ሃማስ ድንበር ዘልቆ በመግባት አብዛኞቹ ሲቪሎች የሆኑባቸው፣ ቁጥራቸው ከ1200 በላይ ሰዎችን የገደለበትን እና ሌሎች 250 ሰዎችን አግቶ የወሰደበትን የመስከረም ሃያ ስድስቱን ጥቃት ተከትሎ በከፈተችው ወታደራዊ ዘመቻ እስካሁን ቁጥራቸው 38 ሺህ የሚደረሱ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚንስቴር ይፋ ያደረገው አሃዝ ያመለክታል።