በመላው የጋዛ ሰርጥ 80 በሚሆኑ ዒላማዎች ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙን የእስራኤል ሠራዊት ዛሬ አስታውቋል። የእግረኛ ጦሩም በምሥራቅ ራፋ በኩል በመዋጋት ላይ መሆኑንም አስታውቋል።
በሰርጡ ደቡብ የምትገኘው ራፋ ከተማ እስራኤል ከሐማስ ጋራ በምታደርገው ጦርነት ዋና ትኩረት ሆናለች፡፡
ከጋዛ ሰርጥ የተነሳው ጥቁር ጭስ ከደቡብ እስራኤል ሆኖ ይታይ ነበር።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ በእስራኤል መከላከያ ኃይል በራፋ አካባቢ የሚደረገው የተባባሰ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳስደነገጣቸው ተናግረዋል። ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ 450 ሺሕ ፍልስጤማውያን በግዳጅ መፈናቀላቸው ተመልክቷል።
አስቸኳይ ሰብዓዊ የተኩስ ማቆም እንዲደረግ እና ታጋቾች በሙሉ እንዲለቀቁ ጉቴሬዝ ጠይቀዋል።
ከጋዛ ነዋሪዎች ውስጥ ግማሽ ያህሉ ከሌሎች የሰርጡ አካባቢዎች በመሸሽ በራፋ ተሰባስበው የሚገኙ ሲሆን፤ የመጠለያ፣ መፀዳጃ እና ንፁህ ውሃ ችግር እንደገጠማቸው ታውቋል።