የሐማሱን መሪ ያህያ ሲንዋርን የገደለችው እስራኤል ዛሬ ጋዛ ላይ ጥቃት አካሂዳለች

ያህያ ሲንዋርን

መሪውን ያህያ ሲንዋርን በመግደል በሐማስ ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሰችው እስራኤል ታጣቂውን ቡድን ለመደምሰስ ላለፈው አንድ ዓመት የያዘችውን ጥቃት ዛሬ አርብም ገፍታበታለች።

የያህያ ሲንዋርን መገደል በማድነቅ የተናገሩት የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ እአአ ጥቅምት ሰባት ሀማስ የቀሰቀሰው ጦርነት አላበቃም ብለው በማስከተል ግን የመጨረሻው መጀመሪያ ነው ብለዋል።

በእስራኤል ታሪክ እጅግ ብዙ ህዝብ የተገደለበትን ጥቃት ያቀደው የሲንዋር መሞት የሀማስን ክፉ አገዛዝ መውደቅ የሚያበስር ምዕራፍ ነው ሲሉ ኔታንያሁ ተናግረዋል።

የእስራኤል ዋና የጦር መሣሪያ ድጋፍ ሰጪ የሆነችው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን "ይህ ቀን ለእስራኤል ፥ ለዩናይትድ ስቴትስ እና ለዓለም ጥሩ ቀን ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ፕሬዚደንት ባይደን በስልክ በሲንዋር መገደል እንኳን ደስ ያለዎ ያሏቸው ሲሆን ሁለቱ መሪዎች አጋጣሚውን በመጠቀም ታጋቾቹን እንዲለቀቁ ብርቱ ግፊት ለማድረግ ቃል መግባታቸውን አመልክቷል።

የእስራኤል የጦር ኅይል "ያህያ ሲንዋር በድሮን ክትትል ሲደረግበት ቆይቶ ግብጽ ድንበር ላይ በምትገኘው የደቡባዊ ጋዛ ራፋህ ከተማ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ተገድሏል " ሲል አስታውቋል።