በደቡብ ሊባኖስ በተደረገ ውጊያ አራት ወታደሮቿ መሞታቸውን እስራኤል አስታወቀች

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ እስራኤል እና ሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ አካባቢ የእስራኤል ወታደር በትራንስፖርት መኪና ላይ ታንክ እየጫነ

በደቡብ ሊባኖስ በተደረገ ውጊያ አራት ወታደሮች መገደላቸውን የእስራኤል ጦር ዛሬ ሰኞ አስታውቋል። ወታደሮቹ ከአንድ ብርጌድ የተውጣጡ መሆናቸውን ያመለከተው ወታደራዊ መግለጫ፣ መቼ እና በምን ሁኔታ እንደተገደሉ ግን አላብራራም።

የእስራኤል ጦር ይህን ያስታወቀው በእስራኤል እና ሊባኖን በሚገኘው የሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን መካከል የተኩስ አቁም ከተደረገው ከሁለት ሳምንታት በኋላ ነው።

የሊባኖስ ጦር በበኩሉ ሰኞ እለት ባወጣው መግልጫ፣ እስራኤል ባካሄደችው የአየር ጥቃት በደቡብ ሊባኖስ በሚገኝ የጦር መከላከያ ኬላ አቅራቢያ አንድ መኪና በመምታት አንድ ሰው ሲገድል፣ አራት ወታደሮች ማቁሰሉን አስታውቋል።

የእስራኤል ባለሥልጣናት ከየመን ተነስቷል ብለው እንደሚያምኑ የገለጹት ጥቃትም በመካከለኛው እስራኤል በምትገኘው ያቭኔ ከተማ የሚገኝ የመኖሪያ ህንፃ ላይ እንዳረፈ ያስታወቁ ሲሆን፣ ስለደረሰው ጉዳት ግን የተገለፀ ነገር የለም።

ሁለቱም ወገኖች ወታደሮቻቸውን ከደቡብ ሊባኖስ ድንበር ለማራቅ ያደረጉት ስምምነት ጦርነቱን በከፍተኛ ደረጃ ቢቀንሰውም፣ አሁንም በአካባቢው ጥቃቶች ይፈፀማሉ።