እስራኤል እና ሐማስ የተኩስ ፋታ ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ

  • ቪኦኤ ዜና
ፍልስጥኤማውያን በማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ በኑሴይራት የስደተኞች ካምፕ በቦምብ ጥቃት የፈረሰውን ሕንፃ እየፈተሹ፣ እአአ ኅዳር 23/2023

ፍልስጥኤማውያን በማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ በኑሴይራት የስደተኞች ካምፕ በቦምብ ጥቃት የፈረሰውን ሕንፃ እየፈተሹ፣ እአአ ኅዳር 23/2023

በእስራኤል እና በሐማስ መካከል፣ ለአራት ቀናት የሚቆየው የተኩስ ፋታ ስምምነት፣ ዛሬ ዐርብ ተግባራዊ መኾን ጀምሯል፡፡

ከወር በላይ ለወሰደው ግጭት፣ ፋታ ይሰጣል የተባለው ይኸው ስምምነት፣ በሐማስ ታጣቂዎች የታገቱትንና በእስራኤል ታስረው ያሉት ፍልስጥኤማውያን የሚፈቱበትን አካሔድ አስቀምጧል።

በእስራኤል፣ የቦምብ ድብደባ እና የመሠረታዊ አቅርቦቶች እጥረት ለደረሰባቸው፣ 2ነጥብ3 ሚሊዮን የጋዛ ነዋሪዎችም፣ ሰብአዊ ርዳታን ለማድረስ ያስችላል፤ ተብሏል።

የእስራኤል ጦር፣ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ፍልስጥኤማውያን፣ አኹንም ወደተወሰኑ አካባቢዎች እንዳይመለሱ ማስጠንቀቁን ቀጥሏል፡፡

በተኩስ ፋታው፣ በጦርነቱ ወቅት የተፈጠሩ የነዳጅ እና የማብሰያ ጋዝ አቅርቦቶችን ለማድረስ እንደተቻለ ቢነገርም፣ ለጋዛ ከሚያስፈልጋት አንጻር እጅግ ውስን እንደኾነ ተመልክቷል፡፡

በካታር፣ በዩናይትድ ስቴትስ እና በግብጽ ሸምጋይነት የተካሔደው የተኩስ ፋታ ስምምነቱ፣ ግጭቱ ውሎ አድሮ እንዲቆም የተስፋ ጭላንጭል እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡

የእስራኤል መሪዎች ግን፣ አስፈላጊ ኾኖ ከተገኘ፣ በጋዛ የሐማስ ታጣቂዎች ላይ እንሰረዝለዋለን፤ ያሉትን ጥቃት ለመቀጠል ዝግጁ እንደኾኑ አስታውቀዋል፡፡

የተኩስ ፋታ ስምምነቱ፣ ተግባር ላይ እንደዋለ ከተገለጸበት፣ ዛሬ ዐርብ ከማለዳው አንድ ሰዓት ጀምሮ፣ ምንም ዐይነት የተኩስ ድምፅ እንዳልተሰማ፣ የአሶሺዬትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

በስምምነቱ መሠረት፣ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 7 ቀን 2023፣ ሐማስ፥ ከእስራኤል አግቶ የወሰዳቸውን 50 ሴቶች እና ሕፃናት ሲለቅ፤ በእስራኤል በእስር ላይ በሚገኙ 150 ፍልስጥኤማውያን ሴቶች እና አዳጊ ሕፃናትም በምላሹ ይለቀቃሉ።