ኢራን በኑክሌር ጣቢያዎቿ ዩራኒየም ማበልፀግ ልትጀምር ነው ተባለ

ኢራን ፎርዶ እና ናታንዝ በተባሉ የኑክሌር ማብላያ ጣቢያዎች በሺሕዎች የሚቆጠሩ የተሻሻሉ የኑክሌር ማብላያዎችን በመጠቀም ዩራኒየም ማበልጸግ ልትጀምር መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኑክሌር ተቆጣጣሪ አካል እንዳለው በጦር መሳርያ ደረጃ ዩራኒየም ማምረቷ፣ በቴህራን የኑክሌር መርሃ ግብር ምክንያት እየታየ ያለውን ውጥረት ያባብሳዋል።

ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ተቋም የወጣው መረጃ፣ ኢራን በአሁኑ ወቅት ዩራኒየም የምታበለጽግበት ጥራት ከማብላያው አቅም በታች መሆኑን ሲያመለክት፣ ይህም ከምዕራቡ ዓለም እና ከመጪው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጋር አሁንም መደራደር እንደምትፈልግ አመላካች ነው ብሏል፡፡

ነገር ግን፣ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በሃማስ ላይ ጦርነት እያካሄደች ባለችበት እንዲሁም በሊባኖስ ከሚገኘው ሄዝቦላህ ጋር የተኩስ አቁም ካደረገችም በኋላም ኢራን አሁንም እስራኤልን ማስፈራራቷን ቀጥላለች። ትራምፕ ሥራ ከጀመሩ በኋላ እንዴት የኢራንን ጉዳይ እንደሚይዙት ግልፅ አይደለም ሲል የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የአራን ልዑክ በአቶሚክ ባልሥልጣኑ ሪፖርት ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ለቀረበለት ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጠም። የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ተቋም ቦርድ ኢራን ከተቋሙ ጋር ሙሉ በሙሉ በመተባበር ላይ አይደለችም በሚል በተጠናቀቀው የፈረጆች ኅዳር ወር ውስጥ ባደረገው ስብሰባ ማውገዙን ተከትሎ ቴህራን በፕሮግራሟ በፍጥነት እንደምትገፋበት ዝታለች፡፡

ኢራን እ.አ.አ. በ2015 ከዓለም ኃያላን ሃገራት ጋር የነበራት የኑክሌር ውል አሜሪካ በእ.ኤ.አ. በ2018 ከስምምነቱ መውጣቷን ተከትሎ ከፈረሰ ወዲህ፣ ከጦር መሳሪያ ደረጃ በታች የሆነ ኑክሌር ማበልፀጉን ቀጥላበታለች።

የአሜሪካ የስለላ ድርጅቶችና የሌሎች ወገኖች ዳሰሳ እንደሚያመለክተው ኢራን የጦር መሳሪያ የማምረት መርሃ ግብር ገና አልጀመረችም።