ኢራን ወደ ኒኩሌር ድርድሩ ልትመለስ ትችላለች

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ የአቶሚክ ምልክት እና የኢራን ባንዲራ ምስል እአአ 8/21/2022

የዛሬ ስድስት ዓመት ከኢራን ጋር የተፈርሞ የነበረውን የኒኩሌር ሥምምነት ለማደስ ወደሚያስችል ድርድር ለመግባት የአውሮፓ ኅብረት ያቀረበው ሀሳብ “የኢራንን ቁልፍ ጥያቄዎች ለማሟላት ማረጋገጫ የሚሰጥ ከሆነ ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል” ሲሉ አንድ የኢራን ከፍተኛ ዲፕሎማት መናገራቸውን የኢራን የዜና ወኪል (ኢርና) ዘገበ።

የዩናይትድ ስቴትስና የኢራን ባለሥልጣናት በስማ በለው ከተነጋገሩበት ቪየና ላይ ለአራት ቀናት ከተካሄደ ንግግር በኋላ “የመጨረሻውን” የሰነድ ቅጂ ባለፈው ሰኞ ማውጣቱን የአውሮፓ ኅብረት አስታውቋል።

ስማቸው ያልተገለፀ አንድ የአውሮፓ ከፍተኛ ባለሥልጣን ‘ለ15 ወራት ድርድር ተካሂዶበታል’ ባሉት ሰነድ ቃል ላይ ካሁን በኋላ ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማይደረግ ጠቁመው በጣም ጥቂት ሣምንታት ውስጥ ከወገኖቹ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ኢርና በስም ያልጠቀሳቸው የኢራን ዲፕሎማት ቴህራን በአውሮፓ ኅብረት የቀረበውን ሀሳብ እያጤነች መሆኑን ገልፀው “ለኢራን ደኅንነትና ማዕቀቦች እንደሚነሱ ዋስትና የሚሰጥ እስከሆነ ድረስ ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል” ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ እንዳደረጉት መጭዎቹ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንቶችም ከሥምምነቱ የማይወጡ ስለመሆናቸው ኢራን ማረጋገጫ እንደምትሻ ተገልጿል።

ይሁን እንጂ ሥምምነቱ ከህግ ይልቅ በፖለቲካ መግባባት የሚደረስበት በመሆኑ ፕሬዚዳንት ባይደን ኢራን የምትፈልገውን የዋስትና ዓይነት መስጠት የማይችሉ መሆናቸው ተጠቁሟል።

የአውሮፓ ኅብረት ያቀረበውን ሥምምነት በፍጥነት በመቀበል ስምምነቱን ለማደስ ዋሺንግተን ፈቃደኛ መሆኗ በዘገባው ተጠቅሷል።