“ተጨማሪ ታጣቂዎች እየገቡ ናቸው”/የማንነት አስመላሽ ኮሚቴው/
የትግራይ ታጣቂዎች፣ ከአከራካሪው የራያ አላማጣ አካባቢዎች ከኾኑት ጋርጃለ እና በቅሎማነቂያ ለቀው እንዲወጡ መወሰኑን፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ አስታውቀዋል።
ውሳኔው የተላለፈው፣ በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሠረት ተፈናቃዮችን ለመመለስ ሲባል እንደኾነ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
የቀድሞው የከተማዋ ከንቲባ እና የራያ ወሎ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኀይሉ አበራ በበኩላቸው፣ የፕሬዚዳንቱ መግለጫ፥ "ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብን ለማታለል ነው፤" ሲሉ ተችተዋል። በአንጻሩ፣ "አሁንም ተጨማሪ ታጣቂዎች እየገቡ ናቸው፤" ሲሉ ከሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በአላማጣ ከተማ፣ የፌደራል የጸጥታ ኀይሎች እንደሚገኙ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ መንግሥት በአስቸኳይ አስተዳደሩን እንዲያዋቅርና ሕዝባዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ጠይቀዋል።