የትግራይ ክልል ምክር ቤት፣ በክልሉ ጊዝያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ የታገዱት እና በቅርቡ በምክር ቤቱ በተሾሙት ከንቲባ ጉዳይ ለመወያየት፣ ለነገ ሐሙስ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. አስቸኳይ ጉባኤ መጥራቱን፣ ከክልሉ ምክር ቤት ዛሬ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።
የከተማዋ ምክር ቤት ከሦስት ሳምንታት በፊት ባሳለፈው ውሳኔ፣ ዶክተር ረዳኢ በርሀ የመቐለ ከተማ ከንቲባ ኾነው እንዲሠሩ ሾሟቸዋል።
ይኽንን ሹመት ተከትሎ የክልሉ የጊዝያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፣ የከንቲባው ሹመት ሕገወጥ ሥልጣን በመያዝ የጊዚያዊ አስተዳደሩን ሥራ ለማደናቀፍ የተደረገ አካሄድ ነው ሲሉ ተቃውሟቸውን በደብዳቤ ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ፣ “ለዶክተር ረዳኢ በርኸ ባሉበት” ብለው በጻፋት እና በክልሉ መገናኛ ብዙኃን በተሰራጨው ደብዳቤ፣ "የመቐለ ከተማ ምክር ቤትን በመጠቀም የአስተዳደሩን ሥራ በማደናቀፍ በተሰማራው ቡድን ተመርጣችሁ ፀረ ጊዝያዊ አስተዳደሩ እየተንቀሳቀሳችሁ ናችሁ” በማለት ከሰዋል።
"የከተማዋ ከንቲባ ተጠሪነቱ ከምክርቤቱ በተጨማሪ ለክልሉ ርእሰ መስተዳደር ነው" ያለው የአቶ ጌታቸው ደብዳቤ፣ "በፀረ ጊዝያዊ አስተዳደር የተሰለፈ በአስተዳደሩ ስር ሆኖ ለመምራት አግባብነት የለውም" ብለዋል።
"ስለዚህም በመቐለ ከንቲባነት ስም ማንኛውም ዓይነት ተግባር እንዳይፈፅሙ፣ ከስራቸው ያለው አመራር ደግሞ በእርሳቸው የሚተላለፍ ማንኛውም ትእዛዝ እንዳይቀበሉ" ሲሉ እግድ አስተላልፈዋል።
የከተማዋ ምክርቤት አስተባባሪ ኮሚቴ ከትላንት በስትያ ሰኞ ባወጣው መግለጫ በበኩሉ ፕሬዝደንቱ ከንቲባውን ማገዱ ተቃውሟል።
አስተባባሪ ኮሚቴው በመግለጫው ምክር ቤቱ ከንቲባ የመሾም የመሻር፣ በጀት የማፅደቅ እና የመቆጣጠር ስልጣኖች እንዳሉት በመጥቀስ ምርጫ እስከሚካሄድ ኃላፊነት እንዳለው ሕጎች በመጥቀስ ጽፏል።
በጊዝያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ የተጻፈው ድበዳቤ የምክርቤቱን ሥልጣን የሚጋፋ በመሆኑ እንዲነሳም መግለጫው ጠይቋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ከክልሉ ምክር ቤት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የጠየቅን ሲኾን፣ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ለነገ ሐሙስ አስቸኳይ ጉባኤ መጠራቱን አስታውቋል።