መንግሥት በሽብር በፈረጀው ህወሃት የሚመራውና ፌደራሉ መንግሥት “መምከኑንና ሥልጣኑ የጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደሆነ” የሚናገርበት እራሱን “የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት” ብሎ የሚጠራው አካል “ዘ ቴሌግራፍ” የሚባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ ላወጣው ዘገባ ባለፈው ሳምንት በሰጠው ምላሽ “በሲቪሎች ላይ የሚፈፀሙ ማንኛቸውንም የጭካኔ አድራጎቶች ያለማወላወል እንደሚያወግዝ” አሳውቆ “መሠረተ ቢስ” ያላቸውን የቴሌግራፍን ዘገባ በብርቱ እንደሚያስተባብል ገልጿል።
መግለጫው አክሎም አማራ ክልል ውስጥ በሲቪሎች ላይ ተፈፅመዋል በተባሉ የወንጀል አድራጎት ክሦች ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚሰየም አካል ነፃ ማጣራት እንዲደረግ ጠይቋል።
ዘ ቴሌግራፍ ከሰሞኑ ባስነበበው ፅሁፍ “የህወሃት ታጣቂዎች በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ የገበሬ መንደሮችን በከባድ መሳሪያ ደብድበዋል” ሲል ዘግቧል። በተለይ “አጋምሳ የተባለውን መንደር ሙሉ ለሙሉ አውድመዋል” ሲል የጉዳቱን መጠን ይተነትናል። ጋዜጣው “የህወሃት ወታደሮች ቤት ለቤት እየዞሩ ነዋሪዎችን ረሽነዋል፤ መኖሪያ ቤቶችን በእሳት እየለኮሱ አቃጥለዋል” ሲል ይገልፃል። “በህወሃት ወታደሮች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር በመቶዎች ይገመታል” ብሏል። የተባለውን አድራጎት “ተጎጅዎችን በማነጋገር፣ የቀደሙና ‘ተፈፀመ’ ከተባለው ጥቃት በኋላ የተወሰዱ የሳተላይት ምስሎችን በንፅፅር በመተንተን ማረጋገጡን” ጋዜጣው ዘግቧል። “ህወሃት ይሄን የፈፀመው በአካባቢው ጦርነት ሳይኖር ሆን ብሎ እና ህዝቡን ለመበቀል ነው” ብሏል ጋዜጣው።
የአማራ ክልላዊ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ግዛቸው ሙሉነህም ባለፈው ሳምንት ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ክልላቸው “ህወሃት አጋምሳ እና አካባቢዋ ላይ “አድርሷል” ያሉትን “ጥቃትና ጅምላ ግድያ” ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን መግለፃቸው ተዘግቧል።
ለዚህ የቴሌግራፍ ዘገባና የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ክሥ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ የትግርኛ ዝግጅት ክፍላችን ባልደረባ በትረ ሥልጣን “እራሱን የትግራይ ክልል መንግሥት” ብሎ የሚጠራው ህወሃት መር አካል የሰሜን አሜሪካ ተጠሪ ናቸው ወደተባሉት ወደ አምባሳደር ፍስሃ አስገዶም ደውሎ ቃለ ምልልስ አድርጓል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡
Your browser doesn’t support HTML5