የኮቪድ ክትባትን የሚደግፉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ተገለጸ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል

በዓለም ዙሪያ በበርካታ ሃገሮች የኮቪድ-19 ክትባት መከተብን የሚደግፉ ሰዎች ቁጥር ቀደም ብሎ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከፍ እያለ መሆኑን አንድ ዓለም አቀፍ ጥናት አመለከተ።

በተለይም ብሪታንያ እና ስዊድን ውስጥ ቁጥሩ መጨመሩን ጥናቱ አመልክቷል። ኬክስት ሲኤንሲ የተባለ የኮሙኒኬሽን ኩባኒያ ዛሬ ባሳተመው ጥናቱ ያካተታቸው ብሪታንያን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ስዊድን እና ዩናይትድ ስቴትስን መሆኑ ታውቋል።

ብሪታንያ ውስጥ ባለፈው መስከረም ወር "መከተቡ ይበጃል" ያሉት ሰዎች ቁጥር ስድሳ አምስት ከመቶ የነበረ ሲሆን አሁን ወደ ሰማኒያ ዘጠኝ ከመቶ ከፍ ማለቱን ጥናቱ አስታውቋል። ስዊድን ውስጥ ደግሞ ቀደም ብሎ ሃምሳ አንድ ከመቶ የነበረው አሁን ወደ ሰባ ስድስት ከመቶ እንዳደገ ነው የጠቆመው።

በዚህ ጥናት መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከወንዶች ስድሳ ስምንት ከመቶ ከሴቶች ደግሞ ሃምሳ አምስት ከመቶው ክትባቱን መውሰድን ይደግፋሉ።

በዩናይትድ ስቴትስ ዜና የሀገሪቱ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል /ሲዲሲ/ አማካሪ ኮሚቴ በጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ኩባኒያ የተሰራው የኮቪድ-19 ክትባት ከአሥራ ስምንት ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች እንዲሰጥ በትናንትናው ዕለት ሙሉ ድጋፉን ሰጥቷል።

የኮሚቴውን ድጋፍ የማዕከሉ ዳይሬክተር ሮሼል ዎሌንስኪ አጽድቀውታል።