Your browser doesn’t support HTML5
ዛሬ በዓለም ላይ፣ ወደ 272 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች አሉ፡፡ ከእነዚህ ከግማሽ ለጥቂት ያነሱት፣ ሴቶች ናቸው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት፣ ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን፣ አገራቸውን ቀይረው በሌሎች አገር የሚኖሩትን እንደ ስደተኞች የሚመለከታቸው ቢሆንም፣ አብዛኞቹ ምክንያታቸው የተሻለ ኑሮና ኢኮኖሚ ፍለጋ እንደሆነም ያምናል፡፡
በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በተገኘው መረጃ መሰረት፣ ከአገራቸው ውጭ በመኖር ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ህንዳውያን ናቸው፡፡ የስደተኞች መዳረሻ በመሆን ዩናይትድ ስቴትስ ትልቁን ድርሻ ስትይዝ፣ ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች ይኖሩባታል፡፡ በመላው ዓለም፣ ወደ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች፣ በኮቪድ 19 ወረርሽ ሳቢያ በተዘጉ ድንበሮች አካባቢ፣ በያሉበት ታግተው ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ ስደተኞችን እየበዘበዙ ወደሌላ አገር የሚያሻግሩ ወንጀለኞችን፣ ወረርሽኙ አላገዳቸውም፡፡
የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ዋና ድሬክተር አንቶኒዮ ቪቶሪኖ “ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር እጅግ አደገኛ በሆነው የሚዲትራኒያን አቅጣጫ በማቋረጥ ወደ ጣልያን የገቡ ስደተኞች ቁጥር በአራት እጥፍ ጨምሯል፡፡ በኤደን ባህረ ሰላጤም በኩል ያየን እንደሆነ አካባቢው ወዳሉ አገሮች ለመድረስ ባህረ ሰላጤውን አገሮች የሚያቋርጡ ወደ 130ሺ የሚሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ የተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ እንኳ አላገዳቸውም፡፡” ይላሉ፡፡
በዚህ ዓመት፣ ከሶስት ሺ አንድ መቶ በላይ የሆኑ ስደተኞች፣ ወደ መዳራሻዎቻቸው አገሮች ከመድረሳቸው በፊት፣ በመንገድ ሞተው ቀርተዋል፡፡ በባህር ውስጥ እየሰጠሙ መቅረት በአብዛኛው የተመለደ ነው፡፡ አብዛኞቹ አገሮች፣ የኮቪድ 19 ክትባትን ለማዳረስ፣ ዝግጁ በሆኑበት በዚህ ወቅት፣ ከዚህ ሁሉ አምልጠው የተገኙ ስደተኞችንም ማካተት እንደሚገባ፣ ቪቶሪኖ ይናገራሉ፡፡
“ በአገሪቱ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ሰዎች፣ ስደተኞች ቢሆኑምን ባይሆኑም፣ ህጋዊ ስደተኞች የመሆን አለመሆናቸው ጉዳይ ከግምት ሳይገባ፣ ሁሉም ክትባቱን ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ቫይረሱ ያስተማረን ነገር ቢኖር፣ እያንዳንዱ ሰው ነጻ ሳይሆን ማንም ሰው ከወረርሽኙ ነጻ ሊሆን አለመቻሉን ነው፡፡”
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ቀን፣ ስደተኞች በስደት በሚኖሩበት አገር፣ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ በማክበር፣ የነሱንም የተሻለ ህይወት፣ የመፈለግ መብት ማክበር እንደሚገባ፣ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እንደሚያምን፣ ድሬክተሩ አቶኒዮ ቪቶሪኖ ይናገራሉ፡፡
“ ስደተኝነት የሰዎች ተፈጥሯዊ ክስተት ነው፡፡ ሁሌም አለ፡፡ በዓለማችንም ላይ እስከመቸውም ይኖራል፡፡”
ስደተኞች፣ ብዙጊዜ የሚታሰቡት፣ እንደ ህገወጥ ሠራተኞች ነው፡፡ አብዛኞቹ ግን፣ በተሰደዱበት አገር የሚኖሩት፣ በህጋዊ መንገድ ሲሆን፣ በሁሉም መስኮች ተሰማርተው ይሰራሉ፡፡ ከጉልበት ሥራ አንስቶ፣ የጤናው እና የቴክኖሎጂውን ዘርፍ ጨምሮ፣ ልዩ ሙያን እስከሚጠይቁት፣ የተለያዩ የሥራ መስኮች ድረስ፣ ተሰማርተው የሚያገለግሉ ናቸው፡፡
በሌላም በኩል የአሜሪካ ድምጽ/ቪኦኤ፣ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ቀን በሚከበርበት በዚህ እለት፣ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣውን፣ የአፍሪካ ስደተኞች ሁኔታ በተሻለ መንገድ እየተከታተለ ለመዘገብ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ ድርጅት ኮሚሽነር፣ ዩ ኤን ኤች ሲ አር ፣ እንዳስታወቀው፣ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት፣ ወደ 50ሺ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን፣ ከሰሃራ በታች ባሉት፣ 18 ሚሊዮን ስደተኞችና ወደ 80 ሚሊዮን ከሚጠጉት የዐለም ስደተኞች ጋር መጨመራቸውንም አመልክቷል፡፡
በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በትግራይ ክልል፣ እየተባባሰ የመጣውን ሰብአዊ ቀውስ፣ በፍጥፍነት፣ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ከሊቢያ ትሪፖሊ እና ምስራታ ከተሞች፣ ከሚሰራጩ የቪኦኤ፣ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች በተጨማሪ፣ በትግርኛ ቋንቋ ስርጭት መጀመሩን፣ የአሜሪካ ድምጽ አስታውቋል፡፡ ስርጭቱ፣ በቅርቡ ከተፈቀናሉ ስደተኞች በተጨማሪ፣ ቀደም ሲሉ በአካባቢው የነበሩትን ኤርትራውያንንም ታሳቢ ያደረገ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
የቪኦኤ ዳይሬክተር ሮበርት ሬይሊ ፣ ቪኦኤ፣ በዓለም ዙሪያ ስደተኞችና ተፈናቃዮችን ጨምሮ በቂ የዜና ሽፋን ለማያገኙ ህዝቦች፣ ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን ለማቀበል፣በቁጠርኝነ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
(ዘገባው በተባበሩት መንግሥታት የቪኦኤ ዘጋቢ ማርጋሬት በሽርነው፡፡)