ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት በኔታኒያሁና የሃማስ መሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ አወጣ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ

የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት /ICC/ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ፣ የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትራቸው ዮአቭ ጋላንት እና የሃማስ ባለሥልጣናትን በጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች በመክሰስ ዛሬ ሐሙስ የእስር ማዘዣ አውጥቶባቸዋል፡፡

የእስር ማዘዣው የወጣው ለ13 ወራት በዘለቀው የጋዛ ጦርነት በእስራኤል በተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች እና እኤአ በጥቅምት 2023 ሀማስ በእስራኤል ላይ ባደረሳቸው የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ ኔታንያሁ እና ጋላንት ሆን ብለው የጋዛን ሲቪሎች እንደ ምግብ፣ ውሃ እና መድሀኒት የመሳሰሉ አስፈላጊ አቅርቦቶችን መከልከላቸውን ሲገልጽ የሃማሱን መሪ መሀመድ ዲፍን ደግሞ እኤአ በጥቅምት 2023 በተፈጸመ ግድያ፣ አግቶ መሰወር፣ ማሰቃየት እና የፆታዊ ጥቃት ወንጀሎች ከሷል። ሃማስ ውሳኔውን ነቅፎታል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኒታኒያሁ ፍርድ ቤቱ በእርሳቸው ላይ ያወጣውን የእስር ማዘዣ አውግዘው፣ እስራኤል “የማይረባ እና የሐሰት ድርጊቶችን ስለምትጸየፍ አትቀበለውም” ብለዋል።

ውሳኔው ኔታንያሁ እና ሌሎቹም በዓለም አቀፍ ወንጀል ተፈላጊ ተጠርጣሪዎች ሆነው እንዲገለሉ ስለሚያደርግ ጦርነቱን ለማስቆም እና ለተኩስ አቁም ድርድር የሚደረገውን ጥረት የበለጠ እንደሚያወሳስበው የአሶሲየትድ ፕሬስ ዘገባው አመልክቷል።

ይሁን እንጂ እስራኤል እና ዋና አጋሯ ዩናይትድ ስቴትስ የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አባላት ስላልሆኑ እና ሁለቱ የሃማስ ባለስልጣናት ቀደም ሲል በግጭቱ ስለተገደሉ የውሳኔ ተግባራዊ አንድምታ ውስን ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማውገዝ እስራኤል ከሃማስ ራሷን የመከላከል መብቷን እንደሚደግፉ ገለጸዋል።

የመብት ተሟጋች ቡድኖች የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ውሳኔ በግጭት የተሳተፉትን አካላት በሙሉ ወደተጠያቂነት ለማምጣት ትልቅ ርምጃ ነው ሲሉ አድንቀዋል፡፡