በኢንዶኔዢያ ዛሬ ረቡዕ በተደረገ ፕሬዝደንታዊ እና የምክር ቤት አባላት ምርጫ 200 ሚሊዮን ሰዎች ድምፅ እንደሰጡ ሲዘገብ፣ በአንድ ቀን ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ድምፅ ሰጪዎች የተሳተፉበት ምርጫ ሆኖ ተመዝግቧል።
በሶስት የሰዓት ዞኖች በምትከፈለውና 17 ሺሕ ደሴቶች ባላት አገር የተደረገው ምርጫ ቆጠራ መጀመሩም ተዘግቧል።
ሁለት የአምስት ዓመታት የሥልጣን ዘመን ያጠናቀቁትን ፕሬዝደንት ጆኮ ዊዶዶን ማን የተካል የሚለው ጥያቄ፣ የመራጮችን ትኩረት የሳበ ነው ተብሏል።
“ምርጫው ዲሞክራሲን የምናከብርበት በዓል ነው። በአቀኝነት፣ በግልጽ እና በነፃ እንደሚካሄድ ተስፋ አለኝ” ሲሉ ተደምጠዋል ተሰናባቹ ፕሬዝደንት፡፡
ሕዝቡ በምርጫው እንደሚያሸንፉ ተስፋ የጣለው፣ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች በዊዶዶ የተረቱት የ72 ዓመቱ የመከላከያ ሚኒስትር ፕራቦዎ ሱቢያንቶ ላይ እንደሆነ በመነገር ላይ ነው። ሱቢያንቶ የዊዶዶን ልጅ በምክትል ፕሬዝደንትነት አጭተዋል። የወቅቱን ፕሬዝደንት ዊዶዶን ተወዳጅነት ለመጠቀም የተዘየደ እንደሆነ ተዘግቧል።
የድምጽ ቆጠራውና የውጤት እወጃው ሳምንታትን ሊወስድ እንደሚችል ታውቋል።