ጥብቅ የሆነው የባይደን በዓለ ሲመት ታዳሚዎችን ይቀንሳል

የዩናይትድ ስቴትስ ነገ ረቡዕ፣ እኤአ ጥር 20፣ የቀጣዩን ፕሬዚደንቷን ጆ ባይደንን በዓለ ሲመት በዋሽንግተን ዲሲ ታከናውናለች፡፡

ሥነ ሥርዓቱ የሚከወነው በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ህንጻ ላይ በተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች የተፈጸመው የአመጽ ጥቃት በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡

አሜሪካውያን ከዚህ ለባሰው ነገር የተዘጋጁ ቢሆንም አንድነታቸን ለመጠበቅ ተስፋ አድርገዋል፡፡ በባይደን በዓለ ሲመት ላይ ይህ እምነት በዋናነት እንደሚንጸባርቅም ተነግሯል፡፡

በአገሪቱ እጅግ አስፈላጊ ለሆነውና በየአራት ዓመቱ አንዴ ለሚደረገው የወግ ሥነ ሥርዓት እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጥበቃ ተዘጋጅቷል፡፡ ዋሽንግተን ከእርስ በርሱ ጦርነት ወዲህ እንዲህ ዓይነቱን የሠራዊት ብዛት አይታ አታውቅም፡፡

ባለፈው ሳምንት የዩናይትድ ስቴትስ ተወካዮች ምክር ቤት ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዲከሰሱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በዚህ መካከል የመጭው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የነገው በዓለ ሲመት፣ “የተባበረች አሜሪካን” መፍጠር ዋነኛ ግቡ ማድረጉ ቀላል ይሆንለት ይሆን? የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡

ከፖሊስ በተጨማሪ እስከ 25 ሺ የሚደርሱ የብሄራዊ ዘብ ወታደሮች ለጥበቃው ተጠርተዋል፡፡ የቀድሞ፣ የምክር ቤቱ ጥበቃ ፖሊስ ኃላፊ የነበሩት፣ ቴረንስ ጌይነር ለአሜሪካ ድምጽ ሲናገሩ፣ የጥበቃው ሁኔታ አስተማማኝ ነው በማለት እንዲህ ብለዋል፡፡

ከዚህ ኦፕሬሽን የተወሰነውን ክፍል እመራ በነበረበት ወቅት፣ ይህ እቅድ ለአንድ ዓመት ያህል ሲካሄድ ነበር፡፡ የጸጥታና ደህንነት አገልግሎት ሠራተኞችን፣ እንዲሁም ከኤፍ ቢ አይና ከምክር ቤቱ ፖሊሶች የተውጣጡትን ኃይሎች ለማገዝ፣ ወደ አምስት ሺ የሚሆኑ ህግ አስከባሪዎችን በአካባቢው ካሉ ወረዳዎች ይመጣሉ፡፡ የሚቀጥለው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት በዓለ ሲመት ያለምንም ችግር እንደሚካሄድ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡

ደህንነቱ የተጠበቀ ሲባል የኮቪድ ወረርሽኙም አካላዊ ርቀት ይመለከታል፡፡ አብዛኛው ሥነ ሥርዓት የሚካሄደው በድረ ገጽ ነው፡፡ ሥነ ሥርዓቱን የሚያጋፍረው ቶም ሃንክስ የተባለው አዝናኝ ባለሙያው ሲሆን፣ ድምጻውያኑ ሌዲ ጋጋ እና ጀኒፈር ሎፔዝም ይጫወታሉ፡፡

እንደወትሮው ባንዲራ ይዘው ለሚመጡ በመቶሺ ዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ግን፣ ዋሽንግተን በአብዛኛው ዝግ ትሆናለች፡፡

በተለያዩ 50 የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች ዋና ከተሞችም፣ ተቃውሞ ስለሚኖር ተጨማሪ ጥበቃው እንደሚኖር ተገምቷል፡፡ በቅርቡ የተሰበሰበው የህዝብ አስተያየት ድምጽ እንደሚያሳየው፣ አንድ ሶስተኛ የሚሆንኑት አሜሪካውያን፣ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ሁከት ሊነሳ ይችላል ብለው እንደሚሰጉ ገልጸዋል፡፡

ካሮላይን የተባሉት አንዲት አሜሪካዊት ሴት ውጥረቱ የተባባሰው ለአገሪቱ ጥያቄዎች ሁሌም መልስ መስጠት በማይፈልጉ ፖለቲከኞች ነው ይላሉ፡፡ እንዲህ ብለዋል

“ሰዎች ብዙ ጊዜ እንወክለዋለን ከሚሉት ማህበረሰብ ጨርሰው የተጠነሉ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ግንኙነት የተበጠሰ ይመስለኛል፡፡”

አውሮፕላን ውስጥ በበረራ አስተናጋጅነት አብረው የሚሰሩት ግን ደግሞ በፖለቲካ አቋም የማያስማሙ ሁለት ሴቶች፣ ሎራ እና ሊንዳ፣ እንዲህ ይላሉ፡፡ እኚህ ሎራ ናቸው

“ቀኙን የሚከተሉ ሰዎች ወደ ቀኝ ርቀው የሄዱ ይመስለኛል፡፡ ወደ ግራ ያዘመሙትም ወደ ግራው መንገድ ርቀው ርቀው የሄዱ ይመስለኛል፡፡”

ሊንዳም ከሎራ በመቀጠል እንዲህ ብለዋል

“ከሷ ጋር የምስማማበት ነገር ይህ ነው፡፡ እንደሚመስለኝ ቀኙ በጣም ቀኝ ግራውም በጣው ወደ ግራ የሄደ ይመስለኛል፡፡”

ባይደን ከሚገጥሟቸው ፈተናዎች መካከል ጠብ አጫሪዋ ሰሜን ኮሪያ አንዷ ነት፡፡ በቅርቡ በአገሪቱ የመንግስት ቴሊቪዥን የታየው የጦር መሳሪያዎችሰልፍ ትርዒት ይህንን ያሳያል፡፡ በአገር ውስጥ ደግሞ፣ እየተባባሰ ያለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ እግጅ የበዛው ሥር አጥነት እና የፖለቲካ ክፍፍሉይገኙበታል፡፡

የኮሌጅ ፕሮፌሰር የሆኑት አንዋር ሀቅ ስለዚህ ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ

“ከአገር ውስጥ ፈተናዎች መካከል፣ እየበዛ ያለው የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ከፍተኛ የሥራ አጥነትና፣ የፖለቲካ ክፍፍል ይገኙበታል፡፡”

ብዙዎች አገራዊ አንድነት እንዲፈጠር ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

የቪኦኤ ዘጋቢ ማይክ ኦሱሊቫንን ካጠናቀረው ከዚህ ዘገባ በተጨማሪ፣ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ በነገው እለት የሚካሄደው በዓለ ሲመት እስከዛሬ ከነበሩት በዐለ ሲመቶች በምን በምን መልኮች እንደሚለዩም አስረድተውናል፡፡

ዝርዝሩን ከተያይዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

ጥብቅ የሆነው የባይደን በዓለ ሲመት ታዳሚዎችን ይቀንሳል