እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን ድብደባ በመቃወም በተለያዩ ሀገራት የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጓል።
በአልጄሪያ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በከተማዋ አልጄርስ እና በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች፣ ፍልስጤማውያንን በመደገፍ እና እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ የምትፈጽመውን ድብደባ በመቃወም ሰልፍ አድርገእዋል።
የአልጄሪያው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ለፍልስጤማውያን ያለውን ድጋፍ ለማሳየት በሚል ላልተወሰነ ግዜ የእግር ኳስ ውድድሩን አቋርጧል።
በጆርዳን፣ ትናንት በጋዛ ሆስፒታል ላይ የደረሰውን ጥቃት በመቃወም የጀመረው ሰልፍ ዛሬም ቀጥሏል።
የአሜሪካ አጋር በሆነችው ጆርዳን፣ በርካታ የፍልስጤም ተወላጆች ይኖራሉ።
በአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና በዓረብ ሀገራት መሪዎች መካከል ጆርዳን ላይ ሊካሄድ ታቅዶ፣ በኋላም የተሰረዘው ስብሰባ፣ ግጭቱን ሊያቆም ይችል ነበር ሲሉ ተንታኞች በመናገር ላይ ናቸው።
በመዲናዋ አማን ትናንት በእስራኤል ኤምባሲ ተሰባስበው ከነበሩት ሰልፈኞች ጋር የተጋጨው የጆርዳን ፖሊስ ዓባላት አብዛኞቹ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።
“በዓረብ ምድር የጺዎናውያን ኤምባሲ ሊኖር አይችልም” ሲሉ ተደምጠዋል ሰልፈኞቹ።
በተመሳሳይ በግብጽ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በትናንትነው ዕለት ከጋዛ ጋር ያላቸውን አንድነት በመግለጽ ሰልፍ ወጥተዋል።
ፍልስጤማውያንን የሚደግፍ ሰልፍ የሚጠሩ ከሆነ “በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይወጣሉ” ሲሉ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት አብደል ፋታአህ አል ሲሲ ተናግረዋል። በግብጽ ሰላማዊ ሰልፍ ክልክል ነው።
በቱዚያም እንዲሁ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች በፈረንሳይ ኤምባሲ ደጅ ላይ በመሰባሰብ ተቃውሞ አሰምተዋል።