የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዩናይትድ ስቴትስ ላይ የሰላ ትችት ሰነዘሩ

  • ቪኦኤ ዜና
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቺን ጋንግ

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቺን ጋንግ

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቺን ጋንግ በዩናይትድ ስቴትስ ላይ የሰላ ነቅፌታ ሰንዝረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን ከያዙ ወዲህ የመጀመሪያቸው በሆነው በዛሬ ማክሰኞ ጋዜጣዊ ጉባዔያቸው እያሽቆለቆለ የመጣውን የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት እና ታይዋንን እንደምትደግፍ በማንሳት ዋሽንግተንን አጥብቀው ነቅፈዋታል።

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ ለራሷ ጥቅም ስትል የዩክሬን ጦርነት እንዲራዘም ስለምትፈልግ የሰላም ጥረቶችን የምታደናቅፍ የሚያስመስል ትችት ሰንዝረዋል።

"የዋሽንግተን የቻይና ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ ከምክንያታዊነት ወጥቷል" ብለዋል የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በዓመታዊው የምክር ቤት ጉባዔ ጎን ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል። አክለውም ዋሽንግተን ቻይናን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እና ለማፈን ብሎም ሁለቱ ሀገሮች በአሸናፊ እና ተሸናፊ ፉክክር እንዲጣመዱ ትፈልጋለች" በማለት ከሰዋል።

"ግጭት ውስጥ እንዳይገባ መከላከያ አጥር ማበጀት ያስፈልጋል የሚሉት ቻይና በቃላትም ሆነ በድርጊት ዘለፋ ወይም ጥቃት ሲሰነዘርባት መመለስ የለባትም ማለታቸው ነው፤ ያ የማይሆን ነገር ነው " ብለዋል።

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አስከትለውም "ዩናይትድ ስቴትስ በተሳሳተ መንገድ በፍጥነት መጓዟን የምትቀጥል ከሆነ ግጭት እና ፍጥጫ መፈጠሩ የማይቀር ነው" ብለው “እንዲህ ያለው ፍጥጫ ኃላፊነት የጎደለው ቁማር ከመሆኑም ሌላ ለሁለቱ ሀገሮች ህዝቦች መሰረታዊ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም የሰው ዘር አይበጅም" ሲሉ ተናግረዋል።

የቻይና እና የዩናይትድ ስቴትስ ግንኙነት ታይዋንን፣ ሰብዓዊ መብት ከበሬታን ንግድ እና ቴክኖሎጂን እንዲሁም ሩስያ ዩክሬን ላይ የከፈተችውን ወረራ በሚመለከት በታሪኩ ባልታየ ደረጃ አሽቆልቁሏል። እናም ቻይና የተለመደውን የጸበኝነት ዲፕሎማሲ ትታ ለዘብ ያለ አቀራረብ መከተሏ አይቀርም የሚሉ ትንበያዎች ነበሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቺን ጋንግ "መቅሰፍት ይመጣል" ወደማለት በሚጠጋ አነጋገር ዩናይትድ ስቲትስ ላይ የሰነዘሩት የበረታ ትችት ፉርሽ ያደረጋቸው ይመስላል።