ኢጋድና ሶማሊያ

ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ጦር እንድታዘምት፣ ኬንያ ደግሞ በዚያ የሚገኝ ሠራዊቷን ከአፍሪካ ሕብረት ጦር ጋር እንድታደናጅ ተጠየቁ፡፡

እየተፍረከረከ ነው የሚባለውን የሶማሊያውን ፅንፈኛ አማፂ ቡድን አልሻባብን ጨርሶ ለመደምሰስ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ለመምከር ስድስት የምሥራቅ አፍሪካ ሃገሮች መሪዎች ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ተሰብስበዋል፡፡

በድርቅና በቸነፈር በደቀቀው የመካከለኛውና የደቡብ ሶማሊያ የተንሠራፋውን የአልሻባብን ጠንካራ ይዞታ ለመሰባበር ሃገሮቹ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ድጋፍ እንደሚሹ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ጦር ምናልባት ኬንያም ወደሶማሊያ ከመግባቷ በፊት ገብቶ የነበረ ሊሆን እንደሚችል ጭምጭምታዎች ይሰማሉ፡፡

ኢትዮጵያ ግን በማስተባበሏ እንደፀናች ነው፡፡

አዲስ አበባ ላይ የተሰበሰቡት የምሥራቅ አፍሪካ መንግሥታት የጋራ ልማት ባለሥልጣን (ኢጋድ) መሪዎች የአልቃይዳውን ግብርአበር አማፂ ኃይል ድል ለመንሣት የሚያስችላቸውን አቅም ለማስተባበርና ጥቃታቸውን ለማጠናከር አልመዋል፡፡

ለዚህም መሪዎቹ ኢትዮጵያ ሠራዊቷን ወደ ሶማሊያ እንድታስገባና ጦሯ እዚያው ደቡባዊ ሶማሊያ ውስጥ አልሻባብን እየደበደበ ያለው ኬንያ ደግሞ ዘመቻዋን ከአፍሪካ ሕብረቱ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ጋር እንድታቀናጅ መጠየቃቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ኬንያ የከፈተችውን ዘመቻ ለመደገፍ መስማማቷን ብሉምበርግ የተባለው የዜና አውታር ዛሬ ዘግቧል፡፡ በዚሁ የብሉምበርግ ዘገባ መሠረት “የኢትዮጵያ መንግሥት ወደሶማሊያ ገብቶ የሠላምና የመረጋጋት ጥረቱን እንዲያግዝ በኢጋድ ተጠይቋል” ሲሉ ባለሥልጣኑ ዋና ፀሐፊ ማሕቡድ ማአሊም ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ “የኢትዮጵያም መንግሥት ይህንኑ ለመፈፀም ቃል ገብቷል” ብለዋል ማሕቡድ ማአሊም፡፡

ዛሬ የወጣ የአሶሺየትድ ፕሬስ ዘገባም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሕብረቱ ኃይል ጦር ልታዋጣ እንደምትችል መጠቆሟን አመልክቷል፡፡

“ኢትዮጵያ ጥያቄውን ግምት ውስጥ ታስገባ ዘንድ አሁን ትክክለኛ ጊዜ ነው “ ብለዋል የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ዲና ሙፍቲ፡፡ “ይሁን እንጂ - አሉ ቃል አቀባዩ - እስከአሁን የደረስንበት ውሣኔ የለም፤ በቅርብ ጊዜ ግን መልስ እንሰጣለን፡፡” - ይላል የኤፒ ዘገባ፡፡

መሪዎቹ በተጨማሪም የአሚሶም አቃበያነ ሠላም በሞቃዲሾና አካባቢዋ ላይ ይዞታቸውን እንዲያጠናክሩ ይፈልጋሉ፡፡ ይደርሣል ተብሎ የሚጠበቀው ተጨማሪ ኃይል፣ የጎሣዎቹ ታጣቂዎችና የሽግግሩ ፌደራል ጦር ተቀናጅተው በሚወስዱት የተጠናከረ እርምጃ መንግሥቱ ቀስ በቀስ ይዞታውን እያሠፋ እንዲሄድ ሁኔታዎችን ያመቻችለታል ተብሎ ታምኗል፡፡

በደቡባዊ ሶማሊያ ከወር በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የኬንያ ጦር ደግሞ በተበላሸው የአየር ጠባይና ስንቅና ትጥቅም እንደልብ ለማስተላለፍና ለማቅረብ ሁኔታዎች በማወካቸው ብዙም የጠቀመ ስኬት አለማስመዝገቡ ይሰማል፡፡

አልሻባብን ድል የመንሣቱ ተስፋ እውን እንዲሆን የውጊያ አቅምን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሣድጉ ሄሊኮፕተሮችን፣ የጦር ጄቶችን፣ ታንኮችን የመሣሰሉ ተልዕኮ ማስፈፀሚያ አቅም ግንባታ መሣሪያዎች እንደሚያስፈልጉ ዲፕሎማቶችና ወታደራዊ ተንታኞች ይመክራሉ፡፡

ይህንን ለማሣካት ታዲያ ፀረ-አልሻባቡ አካባቢያዊ ጥምረት ከአካባቢው አቅም የዘለቀ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ይነገራል፡፡ ይህ ድጋፍ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በዚያ የሚገኘውን የአፍሪካ ሕብረት ጦር ነፃነቶች ማሣደግን ይጨምራል፡፡

በጉዳዩ ላይ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ አጣዳፊ እርምጃ እንዲወስድበት የኢጋድ መሪዎች እንደሚጠይቁ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ሕብረት የኬንያ አምባሣደር ሞኒካ ጁማ ገልፀዋል፡፡

“ስለሰው ቁጥር መናገር ብቻ ጠቃሚ አይደለም፡፡ የአየርና የባሕር ከለላ ሣይኖርህ፣ አስፈላጊውን መሣሪያ ሳትታጠቅ የምድር ለምድር ዘመቻውን ለመንደፍ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ በግንባር ስለምታሠማራው ጦር የምታደርገው ምክክር ስለ ተልዕኮ ማስፈፀሚያ አቅም ግንባታ አቅርቦቶች፣ ስለ መሣሪያና ሌሎችም አስፈላጊ ድጋፎች ከሚደረገው ውይይት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ መሄድ አለበት” ብለዋል አምባሣደሯ፡፡

እነዚህ የምሥራቅ አፍሪካ ሃገሮች በተጨማሪም የአማፂው ቡድን ጠንካራ ይዞታ በሆነው በስልታዊው ኪስማዮ ወደብ በኩል ለአልሻባብ የሚደርሰውን ድጋፍ ለማቁረጥ የሚያስችላቸውን ሥልጣን የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፡፡

ይሁንና “የጦርነት ሁኔታ ወይም ተግባር ነው” የሚሉትን ይህንን መሰሉን ወደብን የመዝጋት ወይም የመቁረጥ እንቅስቃሴ ለመደገፍ የሚያንገራግሩ “አንዳንድ” የተባሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ብርቱ አባላት መኖራቸው ይሰማል፡፡

አምባሣደር ሞኒካ ግን የኪስማዮው የአልሻባብ ስንቅና ትቅጥ አቅርቦች መንገድ መዘጋት ጉዳይ ለዘመቻው መሣካት እጅግ አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን በአፅንዖት ተናግረዋል፡፡ “የአልሻባብ የድጋፍ መንገዶች እስካልተዘጉ ድረስ እነዚህን ፈተናዎች መወጣት ከባድ ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ታዲያ እነርሱ ኪስማዮን የሚቆጣጠሩ በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡ ማቋረጥ ይቻላል ብለን እናምናለን፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤትም በዚህ ጉዳይ ላይ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጠናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡

ከዛሬው ጉባዔ ቀደም ሲል የተካሄዱ ውይይቶች እንደ ፀረ-አልሻባቡ ጥምረት አባልነቷ በኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ መመለስ ጉዳይ ላይ አተኩረው እንደነበር ታውቋል፡፡

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያ ውስጥ ያደረገው ዘመቻ በጎ ስም እንዳላተረፈ፤ ክርስቲያን ሃገር ሙስሊም ሃገርን እንደወረረች ተደርጎ የፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ መሆኑንና በውጤቱም ሁኔታው ለአልሻባብ መጠነ ሰፊ ድጋፍ እንደሸመተለትና አሁንም ኢትዮጵያ ጦሯን ብታስገባ ተመሣሣይ ችግር እንዳይፈጠር የሚሠጉ መኖራቸው ይነገራል፡፡

የመሪዎቹ ጉባዔ አስተናጋጅ ኢትዮጵያ የኢጋድም ሊቀመንበር ስትሆን የዚህ በአልሻባብ ላይ የሚካሄደው ዘመቻና መጠነ-ሰፊው ዕቅድ ዋነኛ አንቀሣቃሽ ነች እየተባለ ነው የሚወራው፡፡

እንዲያውም ኢትዮጵያ ኅዳር 10 ቀን (ባለፈው ዕሁድ ማለት ነው) በመድፍና በታንክ የታጀበ ጦሯን ወሰን ዘልቃ ወደሶማሊያ አስገብታለች የሚል ዘገባ ኒው ዮርክ ታይምስ የሚባለው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚታተመው ዕለታዊ ጋዜጣ ፅፏል፡፡

እንዲያውም እማኞች ነን የሚሉ ነዋሪዎችን ዋቢ ያደረገ አንድ የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ የኢትዮጵያ ወታደሮች ዘልቀው በጋልጋዱድ እና በሂራን ማዕከላዊ አካባቢዎች መታየታቸውን፤ በሩቅ ደቡብ በኩል ደግሞ ቁጥራቸው የበዛ የከባድ ተሽከርካሪዎች ቅፍለቶች የኬንያን ወሰን እያቋረጡ መግባታቸውን አመልክቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ከአዲስ አበባው የመሪዎች ጉባዔ ተመልሰው ሞቃዲሾ የገቡት የሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስትር ሁሴን አራብ ኢሴ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “የኢትዮጵያ ወታደሮች በርግጥ ሶማሊያ ገብተው ከሆነ በፀጋ እንቀበላቸዋለን፡፡” ማለታቸውን ኤኤፍፒ እና ኦል አፍሪካ ዶት ኮም ዘግበዋል፡፡

“ሉዓላዊነታችንን እስካልተጋፋ ማንም ሃገር ቢሆን የአልሻባብን ተዋጊዎች ለመውጋት ጦር ቢያዋጣ በደስታ እንቀበለዋለን፡፡ የአልቃይዳ ግብር አበሮች ከሆኑት ነፍጥ አንጋቾች ጋር እያካሄድን ላለነው ፍልሚያ የዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ ድጋፍ እንሻለን” ብለዋል ሶማሊያዊው የመከላከያ ሚኒስትር፡፡

“የኢትዮጵያ እግር ካልታከለበት የኬንያው ዘመቻ አይሣካም” ብለው የሚያስቡ የጦር ተንታኞች ቢኖሩም በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ግንባር መከፈት ለአልሻባብ “ነፍስ አድን ዜና ነው” የሚሉም አሉ፡፡

ናይሮቢ የሚገኘው ሳውዝሊንክ አማካሪዎች ለተባለ ተቋም የሚሠሩት ሶማሊያዊው የፖለቲካ ተንታኝ አብዲዋሃብ ሼኽ አብዲ ሳመድ “ኢትዮጵያ በራሷ ከምትገባ ይልቅ መንግሥቱን የሚደግፈው የአፍሪካ ሕብረት ሰላም ጥበቃ ኃይል አካል ብትሆን የተሻለ ይሆናል” ሲሉ ይመክራሉ፡፡ “ሶማሊያና ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ባላንጦች ናቸው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያን ለማመን ጊዜ ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም አሁን እያደረጉ እንዳሉት በአሚሶም በኩል ቢመጡ የተሻለ ነው” ብለዋል፡፡

አብዲ ሳመድ ያክሉና ሶማሊያዊያን ጎረቤቶቻቸው ወደሃገራቸው ጦር እያዘመቱ የመሆኑ ጉዳይ እንደሚያሠጋቸው፣ ኬንያና ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶማሊያ ወሰን ከምትጋራቸው ሃገሮች ጋር ውጥረት ውስጥ የኖረች ሃገር መሆኗን ጨምረው ያነሣሉ፡፡

“ወደሶማሊያ ጦር ለማዝመት የተዘጋጁት የግንባር መሥመሮቹ ሃገሮች ናቸው፡፡ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ጥበቃ ኃይል ከጋና፣ ከሲየራ ሌዖን ከናይጀሪያ፣ ከማላዊ እና ከመሣሰሉት ቢመጣ ጥሩ ነበር፡፡ በግንባር መስመር ሃገሮቹ ላይ ግን እሁንም ጥርጣሬ አለ” ባይ ናቸው ተንታኙ፡፡

በተለያዩ መንገዶችም ቢሆን የኢትዮጵያ ኃይል ወደ ሶማሊያ እንዲገባ የአካባቢው ሃገሮች ግፊት እየበረታ መሆኑ ቢሰማም ኢትዮጵያ ግን እስከአሁን ውሣኔ ላይ አለመድረሷን፣ ያስገባችውም ጦር እንደሌለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ ቃል አቀባይ አቶ ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል፡፡

“ኢትዮጵያዊያኑ ወደሶማሊያ ዘልቀው ገብተዋል የሚባለው ዕውነት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ጦር የሚገኘው ድንበር ላይ ነው፡፡ ድንበሩ ቀዳዳ የበዛበት በመሆኑ አንዳንዴ ወታደሮቹ በትክክል የት እንዳሉ ለማወቅ ያስቸግራል፡፡ ይሁን እንጂ ሃቁ፣ አሁን የኢትዮጵያ ወታደሮች የሚገኙት በራሣቸው ድንበር ላይ መሆኑ ነው” ብለዋል፡፡

ኬንያ የአፍሪካ ሕብረት ኃይሎችን ለመቀላቀል ብትወስንም ኢትዮጵያ ግን እየተደረጉባት ያሉትን ግፊቶች የመቀበል አዝማሚያ አይታይባትም የሚሉ አፍሪካ ዲፕሎማቶች አሉ፡፡

ይሁን እንጂ ቃል አቀባይዋ አቶ ዲና ሙፍቲ በዛሬው ጉባዔ ላይ የአካባቢው ሃገሮች መሪዎች የሚያሣልፉት ውሣኔ የመንግሥታቱን ድርጅት እርምጃዎች ጨምሮ እጅግ ፈጣን ምላሽ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ “ንዝህላልነት ወይም ቸልተኝነት አይኖርም” ብለዋል” አቶ ዲና፡፡

ዛሬ ምን ተወሰነ፤ ኢትዮጵያ ምን አለች? ዝርዝሩ እንደደረሰን ይዘን እንመለሣለን፡፡

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡