በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በጃራ መጠለያ ካምፕ የሚገኙ 10ሺሕ የሚደርሱ ተፈናቃዮች፣ ያለምንም የምግብ ርዳታ ለሁለት ወራት በችግር እንደቆዩ ተናገሩ፡፡
ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየታቸውን የሰጡ ተፈናቃዮች፣ በምግብ ርዳታው መቋረጥ የተነሣ ለጤና ችግር እንደተጋለጡና ሕፃናት በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ዘንድ እየሔዱ ለመለመን እንደተገደዱ አመልክተዋል፡፡
የጤና ችግሮቹ በዋናነት ከምግብ እጥረት ጋራ የተገናኙ እንደኾኑ ለአሜሪካ ድምፅ የተናገሩ የጤና ባለሞያ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተፈናቃዩ ላይ፣ ከሥነ ልቡናዊ ቀውስ ጋራ የተያያዙ ጭንቀቶች እና ስጋቶች በስፋት እንደሚስተዋሉ አስረድተዋል፡፡ ማኅበራዊ ቀውሱ ሳይባባስ፣ መንግሥት እና ግብረ ሠናይ ተቋማት ርብርብ እንዲያደርጉም ባለሞያው ጠይቀዋል፡፡
የርዳታ አቅርቦቱ መቋረጡን ያመነው የሰሜን ወሎ ዞን የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ ዓለሙ ይመር፣ ችግሩን ለክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ማስታወቃቸውንና ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡ ኮሚሽን በበኩሉ፣ በተለያዩ አካባቢዎች በሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት ርዳታው በወቅቱ አለመድረሱን አረጋግጦ፣ በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነ ገልጿል፡፡
ለአፋር ክልል አጎራባች በኾነው በዚኹ ጃራ መጠለያ፣ የታጠቁ ኃይሎች እየገቡ ጥቃት እንደሚያደርሱ የጠቀሱት ተፈናቃዮቹ፣ የደኅንነት ስጋትም እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
የዞኑ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት፣ የጸጥታ ችግሩ ስላሳደረው የደኅንነት ስጋት፣ ከአፋር ክልል አመራሮች ጋራ ውይይት መደረጉን አስታውቋል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ያገኛሉ፡፡