የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ /ICRC/ በቅርቡ ሰባት አባሎቹ የተገደሉባቸውን ጨምሮ እየደረሱብኝ ነው ባላቸው ጥቃቶች ሳቢያ በጦርነት በተበታተከችው አፍጋንስታን ያካሂድ የነበረውን የረድኤት እንቅስቃሴ በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ መወሰኑን አስታወቀ።
“ለድርጅቱ እና ለሠራተኞቹ እጅግ ከባድ ስሜት የሚያሳድር ጊዜ ነው።” ያሉት የድርጅቱ ተጠሪ ሞኒካ ዛናሪሊ በዛሬው ዕለት ካቡል ላይ በሰጡት አስተያየት
“በዚያች አገር ካካሄድነው ከሰላሳ ዓመታት በላይ ሳይቋረጥ የዘለቀ ሥራ በኋላ ዛሬ እንቅስቃሴያችንን ለመቀነስ ተገደናል። ይሁን እንጂ አፍጋንስታንን ለቀን የማንሄድ መሆናችንን ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ።” ብለዋል።
ዛናሪሊ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥም ሥራችንን ለማደናቀፍ የሞከሩ የጸጥታ መስተጓጎል የታየባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ካለፈው ታሕሳስ ወር አንስቶ በሰሜናዊ አፍጋንስታን የደረሱን ጥቃቶች ግን የድርጅቱን ሥራ በጠቅላላው ያወኩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በእነኚህ ጥቃቶች ከተገደሉት ውስጥ ስድስት አፍጋንስታናውያን የድርጅቱ ሠራተኞችና ባለፈው ወር በማዛሪ ሸሪፍ ከተማ በሚገኝ ግዙፍ የሕሙማን ማገገሚያ ማዕከል ላይ በደረሰ ጥቃት የተገደሉት የስፓኝ ተወላጅነት ያላቸው የሰላሳ ስምንት ዓመቱ የፊዞትራፒ ባለሞያ ይገኙባቸዋል።
ሎሬና ኤብራል የአጥንት ሕክምና በሚሰጥበት ክፍል ውስጥ አንድ ሕመምተኛ በተኮሰው ጥይት ነው የተገደሉት።