እስራኤል የፍልስጤማውያንን መሬት የመያዟ ጉዳይ በዓለም ዓቀፍ ችሎት በመታየት ላይ ነው

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ ዓለም አቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት ሄግ፣ ኔዘርላንድስ

እስራኤል ለፍልስጤማውያን አገር ምሥረታ የታሰበውን መሬት ለ57 ዓመት የመያዟን ሕጋዊነት በተመለከተ በተመድ ዓለም አቀፍ የፍትህ ችሎት በመታየት ላይ ነው።

በሙግቱ መጀመሪያ ላይ፣ የፍልስጤማውያኑ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሪያድ አል ማሊኪ፣ እስራኤልን የዘር መድልዎ በመፈጸም ከሰዋል። የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም፣ እስራኤል ለፍልስጤማውያን አገር ምሥረታ የታሰበውን መሬት መያዟ ሕገ ወጥ መሆኑን እና በአስቸኳይ እንዲቆም ችሎቱ እንዲወስን ጠይቀዋል።

“ከሃያ ዓመታት በፊት እንደተወሰነው፣ ፍልስጤማውያን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ተጎናጽፈዋል። ሁሉም የተጎናጸፈው መብት ነው። ለድርድር ዩሚቀርብም አይደለም። እስራኤልን ጨምሮ ማንኛውም መሬታችንን የያዘ ኃይል፣ በያዛቸው ሕዝቦች መብት ላይ ያልተገደበ ሥልታን ሊኖረው አይገባም” ብለዋል የፍልስጤማውያኑ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሪያድ አል ማሊኪ።

ችሎቱ የተሰየመው እስራኤል ዌስት ባንክ፣ ጋዛን እና ምሥራቅ እየሩሳሌምን ካለማቋረጥ የያዘችበትን ሁኔታ ለመመልከት ቢሆንም፣ በመካሄድ ላይ ያለው የሐማስ እና እስራኤል ግጭት ወዲያውኑ የችሎቱ ትኩረት ሆኗል ተብሏል።

ከችሎቱ ውጪ ፍልስጤማውያንን የሚደግፉ ሰልፈኞች ባንዲራ እና የተለያዩ ምልክቶችን በመያዝ መፈክር ሲያሰሙ ውለዋል።

ከ50 በላይ አገራት ክርክራቸውን እስከ መጪው ሰኞ ድረስ እንደሚያቀርቡ ታውቋል።

እስራኤል የፍልስጤማውያንን መሬት የመያዟ ጉዳይ፣ ሕጋዊ አስገዳጅነት የሌለው ምክር እና አስተያየት በዓለም አቀፍ የፍትህ ችሎቱ እንዲሰጥበት የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በእ.አ.አ 2022 ጠይቆ ነበር።

ዳኞቹ አስተያየታቸውን ከመስጠታቸው በፊት ለበርካታ ወራት እንደሚመክሩበት ታውቋል።