ሎርድ ሬዚስታንስ የተሰኘው የዩጋንዳ አማፂ ቡድን አዛዥ፣ ጉዳት ላደረሰባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ዩጋንዳዊያን ከ56 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካሳ እንዲከፈላቸው፣ ትላንት ረቡዕ የካቲት 20/2016 ዓ.ም ሄግ የተሰየሙት የዓለምአቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ዳኖች ወሰኑ።
በትዕዛዙ ከተካተቱት ወደ 50 ሺህ የሚጠጉ ተጎጂዎች ውስጥ፣ የቀድሞ ህጻናት ወታደሮች እና ከተደፈሩ እናቶች የተወለዱ ህጻናት ይገኙበታል።
ዶሚኒክ ኦንግዌን በግድያ፣ መድፈር፣ የግዳጅ ጋብቻ እና የህጻናት ወታደር ምልመላን ጨምሮ በተከሰሰባቸው 61 ወንጀሎች ከሦስት ዓመት በፊት ጥፋተኛ ተብሏል።
የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድቤት ይግባኝ ሰሚ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 ዓ.ም መገባደጃ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔውን እና የተፈረደበትን የ25 ዓመት እስር ካፀና በኋላ የካሳ ክፍያ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ወስኖ ነበር።
በዘጠኝ ዓመቱ ለወታደርነት ተጠልፎ የአማፂው አባል የተደረገው ኦንግዌን በተለያዩ ማዕረጎች አልፎ የኃላፊው ጆሴፍ ኮኒ ምክትል ለመሆን በቅቶ ነበር። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ በሰሜናዊ ዩጋንዳ የተፈናቀሉ ሰዎች በተጠለሉባቸው ካምፖች ላይ ለደረሱ ጥቃቶችም ተጠያቂ ነው።
ዋናው ሰብሳቢ ዳኛ ቤርትራም ሽሚት፣ በኦንግዌን የሚመራው አማፂ ተዋጊዎች በሰሜናዊ ዩጋንዳ ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸው አራት ካምፖች ላይ ጥቃት በሰነዘሩበት ወቅት "በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ በተፈፀመ የማይታሰብ ግፍ ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል" ብለዋል።
ችሎት ፊት ያልቀረበው ኦንግዌን ለካሳው ተጠያቂ ቢሆንም፣ ፍርድቤቱ ገንዘቡን ለመክፈል አቅም እንደሌለው በመወሰኑ፣ ካሳው የፍርድ ቤቱ አባል ሀገራት ለተጎጂዎች ከተቋቋም የአደራ ፈንድ እንዲከፈል ውሳኔ አሳልፏል።
ተጎጂዎች እያንዳንዳቸው 812 ዶላር እንደሚያገኙ ዳኛው የገለፁ ሲሆን፣ የቀረው የካሳ ገንዘብ ለማኅበረሰብ መልሶ ማቋቋሚያ መርሃ ግብሮች እንደሚውል ዳኛው ሽሚት ገልፀዋል።