የአሜሪካ መርከብ በሁቲ ሚሳዬል ተመታ

  • ቪኦኤ ዜና

ንብረትነቱ የአሜሪካ የሆነ መርከብ በሁቲ የተተኮሰ ነው በተባለ ሚሳዬል በየመን ባሕረ ሰላጤ ላይ ዛሬ ሰኞ መመታቱ ታውቋል።

ጥቃቱ የመጣው የሁቲ አማፂያን በቀይ ባሕር ወደሚገኝ የአሜሪካ የጦር መርከብ አቅጣጫ ፀረ መርከብ ክሩዝ ሚሳዬል በተኮሱ ከአንድ ቀን ባነሰ ግዜ ውስጥ መሆኑን የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።

የዛሬው ጥቃት “ጂብራልተር ኢግል” በተሰኘችው መርከብ ላይ የተፈጸመ ሲሆን፣ የሁቲ አማፂያን ለጥቃቱ ወዲያውኑ ኃላፊነት አልወሰዱም። ይህም አሜሪካ በሁቲ ላይ ድብደባ ከጀመረች ወዲህ ተፈጥሮ የነበረውንና በቀይ ባሕር ላይ የሚታየውን ውጥረት ያባብሳል ተብሏል።

የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት መፈንዳቱን ተከትሎ፣ ሁቲዎች በቀይባሕር ላይ በሚመላለሱ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸም በመጀመራቸው፣ እስያን እና መካከለኛው ምሥራቅን ከአውሮፓ ጋር የሚያገናኘው የንግድ መሥመር ታውኳል።

ጥቃቱ የተፈጸመው ከኤደን 177 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ እንደሆነ እና መርከቢቱ ከሰማይ በሚሳዬል መመታቷን ካፒቴኑ ሪፖርት ማድረጋቸውን በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ የውሃ አካላት ላይ የሚያተኩረውና ‘የእንግሊዝ የባሕር ላይ ንግድ ክወና’ የተሰኘው ተቋም አስታውቋል።

‘አምብሬይ’ እና ‘ድራያድ ግሎባል’ የተሰኙ የግል የደህንነት ተቋማት ለአሶስዬትድ ፕረስ እንደገለፁት፣ መርከቢቱ ‘ማርሻል አይላንድ’ የተሰኘችውን ደሴት ባንዲራ የምታውለበለብ ዕቃ ጫኝ ስትሆን፣ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ጥቃቱ መፈፀሙን አምኖ የሁቲ አማፂያንን ተጠያቂ አድርጓል።

ሆንም ግን በሰዎች ላይም ይሁን በመርከቢቱ ላይ ይህ ነው የሚባል ከፍተኛ ጉዳት አለመድረሱ እና ጉዞዋን መቀጠሏን ዕዙ ጨምሮ ገልጿል።