ለአፍሪካ ቀንድ አስቸኳይ ዕርዳታ እንዲሰጥ የስደተኞች ኮሚሽኑ ጠየቀ

  • ቪኦኤ ዜና
የቀንድ ከብቶቹ በድርቅ ምክንያት የሞቱበት አርብቶአደር፤ ከጎዴ ከተማ በ80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሃርጉጉዶ ቀበሌ ኢትዮጵያ 08/07/2023

የቀንድ ከብቶቹ በድርቅ ምክንያት የሞቱበት አርብቶአደር፤ ከጎዴ ከተማ በ80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሃርጉጉዶ ቀበሌ ኢትዮጵያ 08/07/2023

በአፍሪካ ቀንድ ለስድስተኛ ወቅት ዝናብ በቀረበት በዚህ ግዜ ከሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ እና ኬንያ የተፈናቀሉና በውሃ በምግብና በደህንነት እጦት የሚሰቃዩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ልመታደግ አስቸኳይ ዕርዳታ እንዲደረግ የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጥሪ አድርጓል፡፡

3.3 ሚሊዮን ለሚሆኑ ስደተኞችና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሕይወት አድን ዕርዳታ ለመሥጠት 137 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ሲል ኮሚሽኑ ጥሪ አድርጓል፡፡

በሶማሊያ ለአሁኑ ረሃብ እንዳይክሰት ለማድረግ ቢቻልም፣ ለሕይወት አስጊ የሆነ የምግብና የውሃ እጥረት እንዳለ የስደተኞች ኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ኦልጋ ሳራዶ ትናንት ጀኒቫ ላይ ተናግረዋል፡፡

ግጭትና ድርቅ አንድ ላይ መከሰታቸው ቀድሞውንም አደገኛ የነበረውን ሁኔታ አባብሶታል ያሉት ቃል አቀባይዋ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ለደህንነታቸው እና ዕርዳታ ለማግኘት ሲሉ መኖሪያቸውን ጥለው ሸሽተዋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያና ሶማሊያ 1.7 ሚሊዮን የሚሆኑ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ኮሚሽኑ ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም 180 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ከሶማሊያና ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያና ኬንያ መሸሻቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

በሶማሊያ ብቻ 287 የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ይገኛሉ፡፡