የአፍሪካ ቀንድ ችግሮች ካልተፈቱ አካባቢው የአሸባሪዎች መናኸሪያ ይሆናል ተባለ

  • ቪኦኤ ዜና

የኮንግረሽናል የምርምር ማእከል የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪ ቴድ ዳኜ በሴኔቱ የውጭ ጉዳዮች ንኡስ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ማብራሪያ ከሰጡት ባለሙያዎቹ አንዱ ናቸው። የአፍሪካ ቀንድ ከሰሀራ በታች ካሉ አገሮች መረጋጋት የማይታይበት አካባቢ መሆኑን የተናገሩት ቴድ ዳኜ፤ ዩናይትድ ስቴይትስ በአካባቢው መረጋጋት እንዲሰፍን በርትታ እንድትሰራ ጠይቀዋል። በጦርነቶች እየታመሰች ያለችው ሶማሊያ ህዝቦቿ ቀያቸውን ጥለው በመሰደድ ላይ ናቸው፤ በርካቶች በየለቱ በማያባራ ጦርነት እየረገፉ ይገኛሉ ሲሉ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ባልተረጋውና ሀገሪቱን ማስተዳደር ቀርቶ ዋና ከተማዋን እንኳን መቆጣጠር ያቃተው የሽግግር መንግስት፣ ስኬት ያጡ አለም-አቀፍ ጣልቃ ገብነቶች ጋር ተዳምረው ለአክራሪዎች በር መክፈታቸውን ቴድ ዳኜ ተናግረዋል።

“በሶማሊያ በርካታ የአሸባሪ ቡድኖች ተፈጥረውል። አልሸባብ፤ የራስ ኮምቦኒ ቡድንና ሂዝቡል ኢስላም፤” ብለዋል።

እነዚህን መሰል ድርጅቶች ለአልቃይዳ ምቹ የመመልመያና እራስን የማጠናከሪያ በርን ይከፍታሉ ሲሉ ቴድ ዳኜ ጨምረው አሳስበዋል።

ኤርትራ ከዩናይትድ ስቴይትስ ጋር ያላት ግንኙነት እየሻከረ መሄዱ እንዳሳሰባቸውም ባለሙያው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ጉዳዮች ደግሞ፤ በቅርቡ የተደረገው የኢትዮጵያ ምርጫ የገዥው ፓርቲን ስልጣን ለማራዘም ሲባል አስቀድሞ የመጫወቻ ሜዳው የተዛባበት ነበር ሲሉ ተናግረዋል።

“በቅድም መርጫ ሂድቱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ታስረዋል ተዋክበዋል-ብሎም ተገድለዋል። ገዥው ፓርቲ የወሰዳቸው እርምጃዎች በአንድ ላይ ባለፉት አመታት የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ብቻ ሳይሆን፤ የማህበረሰብ ተቋማትን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችንና ነጻ የመገናኛ ብዙሀንን ያፈነ ነበር። ከዚያም አልፎ ገዥው ፓርቲ በመንግስት ስር የሚገኙ ቁሳቁሶችንና ንብረቶችን ለምርጫው ተጠቅሟል።”

ክቡር ሊቀ-መንበር፣ ሲሉ የንኡስ ኮሚቴው ሰብሳቢ ኮንግረስማን ዶናልድ ፔይንን የጠሩት የሂውማን ራይት ወች የምስራቅ አፍሪካ መረጃ አጠናቃሪ ሌዝሊ ለፍኮው “ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊት አገር እየሆነች አይደለም፤” ብለዋል።

“ይህን ሀቅ ደግሞ የግንቦቱ ምርጫ አጉልቶ አሳይቷል። እንደሚታወቀው ገዢው ፓርቲ ከ99% በላይ በሆነ ድምፅ አሸንፏል። ከዚህ በላይ ሂውማን ራይትስ ወችን የሚያሳስበው፣ ሥልጣን ጠቅልሎ የመያዝ አዝማሚያ መታየቱ ነው፤” ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚካሄደው የሰብዓዊ መብት እርገጣና ጥቃት አሳሳቢነቱን ገልጸዋል።

“ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በሲቪሉ ማኅበረሰብ ላይ የሚካሄደው የጥቃት እርምጃ እንደ ልምድ ከመወሰዱም በላይ በከፋ ደረጃ እየቀጠለ መሆኑም ያሳስባል። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ወዳጆችን በብርቱ ሊያሳስብ የሚገባ ነው።”

በ1997 የከፈቱት የፖለቲካ መድረኮች ዛሬ ጥርቅም ተደርገው የተዘጉ መሆናቸውን የገለጹት ሌዝሊ ለፍኮው፣ ሂውማን ራይትስ ወች አገሪቱ ውስጥ ባካሄደው ምርመራምና ጥናት መሠረት ያገኘው ውጤት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ዘርፈ ብዙ የማፈኛ ዘዴዎች መጠቀሙን ነው ብለዋል።