የአፍሪካ ቀንድ የድርቅ፣ ረሃብና ፀጥታ የሰሞኑ አጠቃላይ ገፅታ

በኬንያና በሶማሊያ ድንበር አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ የተራድዖውን ሥራ በእጅጉ እየጎዳው መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል፡፡

ካለፈው በቀደመው ሣምንት ወደ ዳዳብ መጠለያ ሠፈሮች ሲጎርፍ የነበረው ስደተኛ ቁጥር እስከ ሦስት ሺህ አራት መቶ ይደርስ ነበር፡፡ ባለፈው ሣምንት የገባው ግን በአጠቃላይ አንድ መቶ ሰው ብቻ ነበር፡፡

የኬንያ መንግሥት 'ወደ ግዛቴ እየገቡ ሰው እየጠለፉብኝ ተቸግሬአለሁ' ባላቸው የአልሻባብ ታጣቂ አማፂያን ላይ ባለፈው ሣምንት ጦር አዝምቷል፡፡

ይህ ወታደራዊ እንቅስቃሴና የጦር ኃይሉ በአካባቢው መከማቸት ሰዉን በእጅጉ እንዳስደነገጠው ይሰማል፡፡ በዚያ ላይ ወደ አካባቢው በመግባት ላይ ያለውን ሰብዓዊ እርዳታ፣ የአቅርቦቱንም እንቅስቃሴ ገድቦታል፤ ጎድቶታል፡፡ ለዚህ የከፋ ረሃብ ተጋላጭ የሆኑ 3 ነጥብ 7 ሚሊየን ሶማሊያዊያን ግን አሁንም አፋጣኝ እርዳታ ሊደርሣቸው ይገባል፡፡

ዙሪያውን በዋጠው ችግር ምክንያት ወደኬንያ ይጎርፍ የነበረው ሰው አቅጣጫውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያዞር ተገድዷል፡፡

ከግጭቶቹ በተጨማሪ ስደተኛውን ከኬንያ እንቅስቃሴው የገደበው በአካባቢው እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ ጭምር መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ቀስ በቀስ እየተበራከተ በሄደው ጠለፋ ምክንያት ኬንያ በአልሻባብ ላይ ጦርነት መክፈቷን የሶማሊያው ፕሬዚዳንት በመቃወማቸው የፓርላማው ምክትል አፈጉባዔ ፋራህ ሞአሊም ደስተኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለተጨማሪ ዝርዝር ዘገባውን ያዳምጡ፡፡