በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ከባድ ተኩስ ተሰማ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ ጁባ፤ ደቡብ ሱዳን

በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ትላንት ሐሙስ ማምሻውን ከባድ ተኩስ እንደነበረ ተገለጸ፡፡

ተኩስ የተሰማው የጸጥታ ኃይሎች የቀድሞ የደኅንነት ኃላፊውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ከተንቀሳቀሱ በኋላ መሆኑን ለተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች ከተላከው የደኅንነት ጥንቃቄ ማሳሰቢያና ከሮይተርስ ዘጋቢዎች ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሀገሩ ሰዓት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ የጀመረው ተኩስ ከየአቅጣጫው አለፍ አለፍ እያለ ለአንድ ሰዓት ያህል ከተሰማ በኋላ መብረዱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ሮይተርስ በጁባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሠራተኞቹ በላከው የጥንቃቄ ማሳሳቢያ ላይ ተኩሱ ከቀድሞ የደህንነት ኃላፊ በቁጥጥር ሥር መዋል ጋራ የተያያዘ መሆኑን እንደተመለከተ ዘግቧል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እአአ ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ የደኅንነት ኃላፊው አኮል ኩር ኩክን ከኃላፊነታቸው እንዳሰናበቱ ተዘግቧል፡፡

ፕሬዝደንቱ ደቡብ ሱዳን እአአ በ2011 ከሱዳን ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ብሔራዊ የደሕንነት ተቋሙን ሲመሩ በቆዩት ኩክ ምትክ የቅርብ አጋራቸውን ሾመዋል።

የሠራዊቱ ቃል አቀባይ ሜጀር ጄኔራል ሉል ሩአይ ኮአንግ የቀድሞ የደሕንነት ሹሙ አለመታሰራቸውን ገልጸው ተኩሱ በተሰማበት ጊዜ ኹሉ መኖሪያ ቤታቸው እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

ቃል አቀባዩ ከሌሎች የደኅንነት ባለሥልጣናት ጋራ ከተነጋገሩ በኋላ ዛሬ ዓርብ ማምሻውን ለጋዜጠኞች መግለጫ እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡

ተንታኞች "የደኅንነት ኃላፊው ከቦታው መነሳታቸው ደቡብ ሱዳን ውስጥ የሥልጣን ፍትጊያ መኖሩን ያመለክታል" ብለዋል፡፡

ኃላፊው የተነሱት ሳልቫ ኪር የሚመሩት የሽግግር መንግሥት በመጭው ታኅሣስ እንደሚካሄድ የገለጸው ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ መራዘሙን ባስታወቀ በሳምንታት ውስጥ ነው፡፡