በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በሐዲያ ዞን ከሰላሣ በላይ ሰዎች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታስረዋል ሲሉ ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተሠማሩ ናቸው የተባሉት ሰዎች የታሰሩት ካለፈው ሣምንት ጀምሮ ሆሳዕና፣ ሾኔና ጎንቦራ ከተሞች ውስጥ መሆኑን ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።
“የታሰሩት በአካባቢው ግጭትና ሁከት እንዲነሳ በማሰብ ብጥብጥ የፈጠሩ ተጠርጣሪዎች ናቸው” ሲል የሐዲያ ዞን የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ምላሽ ሰጥቷል።
በሐዲያ ዞን የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ መሆናቸውን የተናገሩና ለደኅንነታቸው እንደሚሰጉ በመጥቀስ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ አስተያየት ሰጭ ካለፈው ሣምንት አንስቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ አብዛኞቹ ወጣቶች የሆኑ ከሳላሣ በላይ ሰዎች እንደተያዙ ተናግረዋል።
ዞኑ ውስጥ አለ የሚሉትን ብልሹና አድሏዊ አሠራር የሚነቅፉ፣ እኩልነትና ፍትኃዊነትን የሚሰብኩ፣ ሃሣቦችን የሚያንሸራሽሩ፣ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የሚጠይቁ ፀሑፎችን የሚያጋሩ ናቸው”
የታሠሩት “ዞኑ ውስጥ አለ የሚሉትን ብልሹና አድሏዊ አሠራር የሚነቅፉ፣ እኩልነትና ፍትኃዊነትን የሚሰብኩ፣ ሃሣቦችን የሚያንሸራሽሩ፣ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የሚጠይቁ ፀሑፎችን የሚያጋሩ ናቸው” ብለዋል አስተያየት ሰጭው።
ከታሰሩት መካከል መለስ አብርሐም የሚባሉ በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፖሎጂ መምህርና "ሐዲያ ሚዲያ ሐውስ" የሚባል የዩትዩብ ሚድያ መሥራች እንደሚገኙበት ተገልጿል።
አቶ መለስ የአፈር ማዳበሪያ እጥረትንና የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ በወቅቱ አለመከፈልን የመሣሰሉ መልዕክቶችን እንድሚያንሸራሽሩ በዚህ ምክንያትም ከዞኑ አስተዳደርና ከክልሉ መንግሥት ማስፈራሪያና ዛቻ ይደርሷቸው እንደነበረ አቶ መለሠ ራሣቸው ባለፈው ሣምንት ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረው ነበር።
የሐዲያ ዞን የሰላም እና ፀጥታ መምራያ ኃላፊ አቶ ሣሙኤል ሽጉጤ “መደዳ ወይም የዘፈቀደ እሥራት እየተካሄደ ነው” መባሉን አስተባብለው በአካባቢው በግጭትና በሁከት የተጠረጠሩ ሰዎች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መታሰራቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
በህግ የሚፈለጉ ሰላሣ ሰባት ሰዎች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታስረው እንደነበር ለአሜሪካ ድምፅ የገለፁት የመምሪያው ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ አሥራ ሦስቱ መለቀቃቸውንም አስታውቀዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዚዳንት እንዳሻው ጣሰው ከሁለት ሣምንት በፊት በአንድ ስብሰባ ላይ ሲናገሩ የሃዲያ ዞንን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች "የመንግሥት ባለሥልጣናት ሥራቸውን እንዳይሠሩ ያደርጋሉ" ያሏቸው 276 ወጣቶች በቁጥጥር ሥር እንደሚውሉ ጠቁመው ነበር።