በሱዳን የዴሞክራሲ አቀንቃኞች ሰልፍ አደረጉ

ሰልፈኞች በወታደራዊው መንግሥት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ሲገልጹ ካርቱም፣ ሱዳን

በሱዳን፣ በሲቪሎች የሚደረገው የተቃውሞ እንቅሰቃሴ ታሪካዊ ቀን በኾነበት በትላንትናው ዕለት፣ ሰልፈኞች በወታደራዊው መንግሥት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ሲገልጹ ውለዋል፡፡ ለዐሥርት ዓመታት፣ በወታደራዊ አገዛዞች ላይ ሲደረግ የቆየው ተቃውሞ፣ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙ ኹለት መሪዎችን ያስወገደበት ቀን፣ ትላንት ታስቦ ውሏል።

የትላንቱ ሰልፍ የተደረገው፣ በታቀደው የዴሞክራሲ ሽግግር ውስጥ ጦሩ የሚኖረውን ድርሻ በተመለከተ መከፋፈል ይስተዋላል፤ የሚሉ ሪፖርቶች እየወጡ ባሉበት ወቅት ነው። ክፍፍሉ፣ የሽግግር መንግሥቱ ሥራ የሚጀመርበትን ጊዜ እንዲራዘም አድርጓል።

ትላንት ሰልፉ እንደሚካሔድ አስቀድመው ያወቁ ባለሥልጣናት፣ በዕለቱ ሥራ እንዳይኖር ዐውጀዋል፡፡ ከረቡዕ ጀምሮ ከፍተኛ የጸጥታ ኃይል በመዲናዋ ካርቱም መታየቱን፣ ትዕይንቱን የታዘቡ ተናግረዋል።

“ወታደሩ ወደ ካምፑ ይመለስ!” እና “ሕዝቡ የሲቪል መንግሥትን ይሻል!” የሚሉ መፈክሮች፣ በትላንትናው ሰልፍ ላይ ተደምጠዋል።

በኦምዱርማን እና ፖርት ሱዳን በተደረጉት ሰልፎች ላይ፣ የጸጥታ ኃይሎች በመቶ በሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ላይ፣ አስለቃሽ ጋዝ ተኩሰዋል፤ ሲሉ የዐይን እማኞች ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

ከአራት ዓመታት በፊት በዐመፅ የተወገደውን የኦማር አል በሺርን አገዛዝ በተካው የሽግግር መንግሥት ላይ መፈንቅለ መንግሥት በማድረግ፣ በጄኔራል አል ቡርሃን የሚመራ ወታደራዊ አገዛዝ ላለፉት ኹለት ዓመታት በሱዳን ሥልጣኑን ተቆጣጥሯል።