የግሪክ ፖሊስ ህገወጥ ያላቸውን 92 ፍልሰተኞች ከቱርክ ጋር በሚያዋስነው ድንበር ላይ ባለፈው አርብ ዕለት ራቁታቸውን ማግኘቱን አስታውቋል። አንዳንዶቹም ሰውነታቸው ላይ ጉዳት እንደሚታይ ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።
ፍልሰተኞቹ ሁሉም ወንዶች ሲሆኑ፣ በግሪክና በቱርክ ድንበር መካከል በሚገኝ ኤቭሮስ በተባለ ወንዝ አቅራቢያ መገኘታቸው ታውቋል።
ፍልሰተኞቹ ልብሳቸውን በምን ሁኔታ እንዳጡ ለጊዜው ማወቅ አልተቻለም።
የግሪክ የተኞች ሚኒስትር ኖቲስ ሚታራቺ በትዊተር መልዕክታቸው፣ ቱርክ ፍልሰተኞችን የምትይዝበት ሁኔታ “በዚህ የሥልጣኔ ዘመን አሳፋሪ ድርጊት ነው” ብለዋል። አቴንስ ጉዳዩን በተመለከተ አንካራ ምርመራ ታደርጋለች ብላ ትጠብቃለች ሲሉ አክለዋል።
የቱርክ ባለሥልታናት በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ለማድረግ ወዲያው ማግኘት አልተቻለም።
ግሪክ በእአአ 2015 እና 2016 የአውሮፓ ፍልሰተኞች ቀውስ ማዕከል ሆና ነበር። አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልሰተኖች ከሦሪያ፣ ኢራቅና አፍጋኒስታ ጦርነትን በመሸሽ በቱርክ አድርገው ግሪክ ገብተው ነበር።
አዲስ የሚመጡት ፍልሰተኞች ቁጥር ከዛ ወዲህ የቀነሰ ቢሆንም፣ በቅርብ ግዜያት ግን በቱርክ ድንበር በኩል የሚመጡ ፍልሰተኖች ቁጥር እየጨመረ ነው ሲሉ የግሪክ ባለሥልጣናት ይገልጻሉ።
ግሪክ የ2016ቱን ከአውሮፓ ህብረት ጋር የተደረገውንና፣ የሚመጡትን ፍልሰተኞች እዛው እንድታቆይ አንካራን የሚጠይቀውን ሥምምነት ቱርክ እንድታከብር ጠይቃለች። ሥምምነቱ በቢሊዮን ዩሮ የሚቆጠር ዕርዳታ ለቱርክ እንደሚያስገኝ ይገልጻል።
ቱርክ በበኩሏ ሕገ-ወጥ የሰዎች አስተላላፊዎችን በተመለከተ ጠንከር ያለ ሥራ እየሰራች መሆኑን ትገልጻለች።