ዓለም አቀፍ የጭነት መርከብ ድርጅቶች የቀይ ባህር መስመሮችን መሸሽ ቀጥለዋል

የመን ካርታ

የዴንማርክ የመርከብ ኩባንያ ማርስክ እና የጀርመኑ ተፎካካሪው ሃፓግ-ሎይድ በቀይ ባህር ላይ የሚገኙ የየመን ሁቲ ታጣቂዎች በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በሜርስክ መርከብ ላይ ባደረሱት ጥቃት ምክንያት የኮንቴይነር ጭነት አጓጓዥ መርከቦቻቸውን ከቀይ ባህር መስመር አርቀው ለማቆየት መወሰናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የሁቱ ታጣቂዎች በቀይ ባህር የጭነት መርከቦች ላይ በሰነዘሯቸው ጥቃቶች ሳቢያ፣ ሁለቱ ግዙፍ የመርከብ ድርጅቶች፣ የአንዳንዶቹን መርከቦቻቸውን መስመር በአፍሪካ ደቡባዊ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በኩል በማዞር ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ይህ የጉዞ መስተጓጎል በእቃዎች የማጓጓዣ ዋጋ ላይ እንዲሁም ገና አዲስ የሆነውን ዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት የሚያባብስና የሸቀጦች ዋጋ እንዲወደድ ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት አስከትሏል፡፡

የሁቲ ታጣቂዎች ወደ ማርስክ ሃንግዙ መርከብ ለመሳፈር መሞከራቸውን ተከትሎ ማርስክ ባላፈው እሁድ በቀይ ባህር ላይ የተሰማሩ ሁሉም መርከቦች ጉዟቸውን ለ48 ሰዐታት እንዲያቆሙ አድርጓል፡፡

ጥቃቱን ለመቀልበስ በስፍራው የተሰማሩት የዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ ሂሊኮፕተሮች 10 ታጣቂዎችን ገድለዋል፡፡

ሜርስክ የመርከብ ድርጅት በሰጠው መግለጫ "ክስተቱን አስመልክቶ የሚደረገው ምርመራ በመካሄድ ላይ ሲሆን ፣ በየጊዜው እየተለወጠ ያለውን ሁኔታ እየገመገምን፣ በአካባቢው ያሉንን ሁሉንም የጭነት እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረጉን እንቀጥላለን" ብሏል፡፡

ሜርስክ በስዊዝ ካናል መተላለፊያ በኩል ቀይ ባህርን አቋርጠው የሚጓዙ ከ30 በላይ ኮንቴይነር ተሸካሚ መርከቦች ያሉት ድርጅት ሲሆን ባላፈው ሰኞ 17 የሚሆኑት መርከቦቹን እንዲቆሙ ማድረጉትን አስታውቋል፡፡

የስዊዝ ካናል መተላለፊያ በግምት አንድ ሶስተኛው የዓለም የጭነት ተሸካሚ ኮንቴይነሮች ይተላለፉበታል፡፡

ጭነቶችን ከዚህ መስመር በመቀየር በአፍሪካ ደቡብ ጫፍ በኩል አድርጎ እንዲጓጓዙ ማድረግ ከእስያና ሰሜን አውሮፓ መካከል ለሚደረገው አንድ ዙር ጉዞ እስከ 1 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ የሚችል ተጨማሪ የነዳጅ ዋጋ እንደሚያሰወጣ ተገምቷል፡፡