የጋና ሕግ አውጪ ምክር ቤት፣ የሞት ፍርድ ቅጣትን፣ ከሕግ መድበሉ እና ሥርዐቱ ቀሪ ለማድረግ ድምፅ እንደ ሰጠ፣ የምክር ቤቱ አባላት፣ ዛሬ ረቡዕ ተናገሩ፡፡
ሕግ አውጭዎቹ፣ የሞት ቅጣትን ከአገሪቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ እንዲወገድ የወሰኑት፣ ትላንት ማክሰኞ ማምሻው ላይ እንደኾነ ተነግሯል፡፡
ውሳኔው፣ በሁሉም ወንጀሎች ሊባል በሚችል መልኩ፣ የሞት ቅጣትን ከሕጋቸው ቀሪ ከአደረጉ የአፍሪካ ሀገራት፣ ጋናን የቅርብ ጊዜ ተጨማሪ እንደሚያደርጋት ተነግሯል፡፡
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋና፣ ለመጨረሻ ጊዜ የሞት ፍርድ ቅጣት ተግባራዊ ያደረገችው፣ እ.ኤ.አ. በ1993፣ ለግድያ እና ክሕደት በተሰጠው ውሳኔ እንደኾነ ተመልክቷል፡፡
የተላለፈባቸው የሞት ቅጣት ተፈጻሚነት በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ 172 ፍርደኞች፣ ውሳኔው ወደ ዕድሜ ልክ እስራት እንደሚቀይርላቸው፣ የጋና ማረሚያ ቤት አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የመብት ተሟጋቹ ቡድን አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ “ትልቅ ርምጃ ነው፤” ሲል ውሳኔውን አድንቋል፡፡ከ55 የአፍሪካ አገሮች 23ቱ፣ የሞት ቅጣት፣ ከሁሉም የወንጀል ዐይነቶች እንዲቀር መወሰናቸውን፣ አምነስቲ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡