በጋና ነገ ቅዳሜ ለሚደረገው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ሁለቱ ዋና ተፎካካሪ ዕጩዎች ትላንት ሐሙስ ምሽት በመዲናዋ አክራ የምርጫ ዘመቻ ሰልፍ አካሂደዋል።
በካካዎ ወይም ኮኮ ምርቷ በዓለም ሁለተኛ ደረጃን የያዘችው ጋና፣ ነገ በምታካሂደው ምርጫ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ዓባላትንም ትመርጣለች፡፡
የዋናው ተቃዋሚ ፓርቲ ‘ናሽናል ዲሞክራቲክ ኮንግረስ’ መሪ የሆኑት የቀድሞ ፕሬዝደንት ድራማኒ ማሃማ፣ በመቶ ለሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር፣ ምርጫው ሃገሪቱን ወደ ትክክለኛ አቅጥጫ ለመመለስ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ቅድመ መርጫ የሕዝብ አስተያየት መመዘኛዎች ወደ ድራማኒ ማሃማ ያመዘኑ መሆናቸውን ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል። ጋና ለገጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ ተፎካካሪያቸውና የገዢው ፓርቲ ወኪል የሆኑትን ምክትል ፕሬዝደንት ማሃማዱ ባዉሚያ ተጠያቂ አድርገዋል።
ባውሚያ በበኩላቸው በጠሩት ሰልፍ ላይ፣ ኢኮኖሚው በመሻሻል ላይ መሆኑን ተናግረው ከተቀናቃናቸው የአስተዳደር ዘመን አንፃር የተሻለ ኢኮኖሚና የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ ተናግረዋል።