ጋና በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁሮችን ወደ ሀገሯ እንዲመጡ በመጋበዝ ላይ ስትኾን፣ በቅርቡም 524 ለሚሆኑና በአብዛኛው ጥቁር አሜሪካውያን ለኾኑ ሰዎች ዜግነት ሰጥታለች።
ጋና ከአምስት ዓመታት በፊት “የመመለስ ዓመት” የሚል ተነሳሽነት ከጀመረች ወዲህ የተሰጠ ከፍተኛው የዜግነት ቁጥር መሆኑም ታውቋል። ተነሳሽነቱ የመጀመሪያዎቹ አፍሪካውያን በበባሪያ ፍንገላ በ1619 ዓ.ም ወደ አሜሪካ የመጡበትን አራት መቶኛ ዓመት ለማሰብ ያለመ ነው።
ከረጅም ጊዜ በፊት የተሰበረው ቁርኝት መልሶ በመጠገኑ ሰዎች እጅግ ሲደሰቱ መስተዋሉን የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።
በዜግነት አሰጣጥ ሥነ ሥርዐት ላይ አንዳንዶች የጋናን ባንዲራ በማውለብለብ በደስታ ሲያለቅሱም ተሰተውሏል። ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካ ሳሉ ያልተሰማቸው ደስታና የማንነት ስሜት እንደተሰማቸውም አንዳንዶች ተናግረዋል።