የጀርመኑ የገና ገበያ ጥቃት ፖለቲካዊ ውዝግብ አስከትሏል

ባለፈው ዐርብ በጀርመን ትውልደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሆነ ግለሰብ ወደ አንድ የገና ገበያ መኪናውን በመንዳት ቢያንስ አምስት ሰዎችን መግደሉን ተከትሎ፣ ነዋሪዎች ሀዘናቸውን ለመግለጽ አበቦች እና ሻማዎች እያስቀመጡ፤ ማግደቡርግ፣ ጀርመን፣ እአአ ታኅሣሥ 22/2024

ባለፈው ዐርብ በጀርመን ትውልደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሆነ ግለሰብ ወደ አንድ የገና ገበያ መኪናውን በመንዳት ቢያንስ አምስት ሰዎችን መግደሉን ተከትሎ፣ በሀገሪቱ በደኅንነትና ፍልሰተኞች ጉዳይ ላይ የነበረው ሙግት አገርሽቷል።

ሀገሪቱ በሚቀጥለው መስከረም ለምርጫ እየተዘጋጀች መኾኑ ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አነጋጋሪ አድርጎታል።

ባለሥልጣናት ጥቃቱ እንዳይፈጸም ተጨማሪ ጥረቶች ማድረግና ማስጠንቀቂያም መስጠት ነበረባቸው የሚለውም አነጋጋሪ ሆኗል።

ታሌብ ኤ. በሚል የሚጠራውና ትውልደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሆነው የ50 ዓመት ተጠርጣሪ የሥነ ልቦና ባለሞያ መሆኑ ሲታወቅ፣ ፀረ እስልምና ቅስቀሳ በማድረግና በጀርመን የቀኝ አክራሪው ‘አማራጭ ለጀርመን’ ወይም ኤ ኤፍ ዲ ፓርቲ ደጋፊነቱ ይታወቃል። ግለሰቡ ለግድያው ምን እንዳነሳሳው እስከ አሁን አለመታወቁን ዘገባዎች አመልክተዋል። የኤ ኤፍ ዲ ፓርቲ ግድያው በተፈፀመበት ማግድበርግ ከተማ ዛሬ ማምሻውን ሰልፍ ጠርቷል። ፓርቲው በፀረ ስደተኞች አጀንዳ በመንቀሳቀስ ላይ ሲሆን፣ በሕዝብ አስተያየት መለኪያ በምርጫ ፉክክሩ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።

ሳዑዲ ዓረቢያ ባለፈው ዓመት ግለሰቡን በተመለከተ ለጀርመን መረጃ አቀብላ የነበረ ሲሆን፣ የጀርመን የስለላ ባለሥልጣናት ምርመራ አድርገው ያገኙት ነገር እንደሌለ አስታውቀው ነበር።

በሌላ በኩል ብሬመርሃፈን በተባለች የጀርመን ከተማ ዓረብ የሚመስሉ ሰዎች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽም በቲክ ቶክ ያስታወቀን ግለሰብ ፖሊስች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል።