ጀርመን ቻይና ሩሲያን መደገፏን እንድታቆም ጠየቀች

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ጂንግ፣ ቻይና

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ቤጂንግ ለሞስኮ የምታደርገውን ድጋፍ ግንኙነታቸውን እንደሚያሻክር በመግለጽ ቻይና የዩክሬንን ግጭት ለማስቆም እንድታግዝ የቻይና አቻቸውን አስጠንቅቀዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ይሄንን ያሉት በቤጂንግ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡ አናሌና ከአንድ ሺህ ቀናት በላይ የፈጀው ጦርነት አለምን ሁሉ እየጎዳ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በጦር ሜዳ ያላቸውን ሚና እና በግጭቱ በቻይና የተሰሩ ድሮኖች ጥቅም ላይ መዋላቸውን አውግዘዋል፡፡

አናሊና ቤርቦክ “ዛሬ ቻይና ያለሁት ለዚሁ ነው” ያሉ ሲሆን ሁሉም የመንግስታቱ ድርጅት ቋሚ የጸጥታው ምክርቤት አባል “ለአለም ሰላም እና ደህንነት ሃላፊነት አለበት” በማለት ተናግረዋል፡፡

በርሊን ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከቻይና ጋር የተሻለ ግንኙነት ለመፍጠር በምታደርገው ጥረት የጀርመኗ ከፍተኛ ዲፕሎማት ከአቻቸው ዋንግ ዪ ጋር “ስልታዊ ውይይት” ለማድረግ ተገናኝተዋል።

ዋንግ ለጀርመን አቻቸው “የዓለም ሁለተኛ እና ሦስተኛ ትልቅ ምጣኔ ሃብት ባለቤት” እንዲሁም “በነውጥ ውስጥ ባለው ዓለም አቀፍ ሁኔታ ውስጥ እንደ ታላላቅ ኃያላን" ሃገራት ቻይና እና ጀርመን ግንኙነታቸውን ማሻሻል አለባቸው ብለዋል፡፡