ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ማኅበራት በኅዳሴ ጉዳይ

ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ውኃን የመሙላት ሥራ በሁለት ሣምንታት ውስጥ እንደሚጀመር፣ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከልም በአሞላልና በአተገባበሩ ላይ በዚሁ ጊዜ ውስጥ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ከተገለፀ አንድ ሣምንት ተቆጠረ። በግድቡ ዙሪያ የቀጠለው ንግግር በምሁራን ዘንድም መነጋገሪያ ሆኗል። ባለፈው ሳምንት ውስጥ ከአሜሪካ ድምፅ ጋር የተነጋገሩ በካይሮው አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ መምህር ፕሮፌሰር ሰዒድ ሳዲቅ ውኃውን የመሙላትን ጉዳ ማዘግየት እንደሚሻል አስተያየት ሰጥተዋል። ካለበለዚያ የግብፅ መንግሥት ወታደራዊ እርምጃ እንዲወስድ የውስጥ ግፊት እንደሚያይልበት፣ ይሁን እንጂ ማንም ባለሥልጣን ያንን አማራጭ አንስቶ ሲናገር አለመስማታቸውንም ገልፀዋል። የኢትዮጵያን ውሣኔ ሊያስቀየር የሚችለውም በመንግሥታቱ ድርጅት የምጣኔ ኃብት ማዕቀብ ቢጣልባት እንደሆነ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ግብፅ ውስጥ ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ከመንግሥቱ አካባቢና ከባለሃብቶችም ይሰማል የሚሉትን መነሻ በማድረግ የግብፅ የወረራ ሃሣብ አሳቦናል ያሉ በዳያስፖራ የሚገኙ 15 የኢትዮጵያዊያንና የትውልደ ኢትዮጵያ ባለሙያዎች፣ ምሁራንና የሲቪክ መብቶች ተሟጋች ማኅበራትና ድርጅቶች ለኢትዮጵያ መንግሥት ጥረቶች ያላቸውን አድናቆትና ድጋፍ ገልፀው ኢትዮጵያዊያን ማንኛቸውንም ልዩነቶቻቸውን አስወግደው ከመንግሥቱ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በግርጌ ሃገሮች ላይ የጎላ ጉዳይ ሳይደርስ የአባይ ውኃን የተካከለና ፍትኃዊ አጠቃቀም ተግባራዊ ለማድረግ የሚቻልበትን መላ ለመፈለግና ወገኖቹን ለማግባባት እንዲተጉ የሚያሳስብ ባለ ስድስት ነጥብ ጥያቄ አቅርበዋል።

ከግብፃዊው ፕሮፌሰር ሰዒድ ሳዲቅ ጋር የተደረገውን ቃለምልልስ መሉ ዘገባ አቅርበን ኢትዮጵያዊያኑ ድርጅቶችና ማኅበራት ያወጡትን መግለጫ ካረቀቁት ምሁራን አንዱ የሆኑትን በደቡብ አፍሪካ ዊትዋተርስትራንድ ዩኒቨርሲቲና በአሜሪካም ዴንቨር ስቴት ዩኒቨርሲቲ መምህር ከሆኑት ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ ጋር ያደረግነው ሙሉ ቃለ ምልልስ ከዚህ በተያያዘው የድምፅ ፋልይ ላይ ይገኛል፤ ያድምጡት።

Your browser doesn’t support HTML5

ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ማኅበራት በኅዳሴ ጉዳይ