ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብን በመሙላትና በአተገባበሩ ላይ ያሉ ጉዳዮችን አስመልክቶ ሦስቱ ሃገሮች የሚግባቡበት ስምምነት ላይ በሁለት ሣምንታት ውስጥ እንዲደርሱና የተናጠል እንቅስቃሴ እንዳይደረግ ለማቆም እንዲቻል ሲሉ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ሰሞኑን ጥያቄ አቅርበዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምፅ በደረሱበት አቋም ጉዳዩን የአፍሪካ ኅብረት እንዲይዘውና ሃገሮቹ ወደ ንግግሮቻቸው እንዲመለሱ ተስማምተዋል። የኢትዮጵያም አቋም ይኸው ነው።
ስምምነት መደረስ ይቻል ይሆን?
በካይሮው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካዊ ኅብረተሰብ ጥናት መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሰይድ ሳዲቅ ከአሜሪካ ድምፅ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ በገለፁት ሃሳባቸው “አሁን ባለው አካሄድ ስምምነት ላይ የሚደረስ አይመስላቸውም።”
በእርሳቸው እምነት “ባለፉት አሥራ ሦስት ዓመታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ እራቅንና ሊብያን ለመሣሰሉ ሃገሮች ያወጣቸውን ውሣኔዎች እንኳ ማስፈፀም አልቻለም፤ አካባቢያዊ ኅብረቶችም ደካሞች ናቸው።”
ፕሮፌሰር ሳዲቅ ይልቅ የሚያነሱት ሃሣብ “ኢትዮጵያ ሃሣቧን እንድትለውጥ ለማስገደድ የምጣኔ ኃብት ማዕቀብ ሊጣልባት ይገባል።”
በሌላ በኩል ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥና ከአሜሪካ ውጭም ያሉ የኢትዮጵያዊያንና ተውልደ ኢትዮጵያ የማኅበረሰቦች፣ የሲቪክ መብቶችና የኅዳሴ ግድብ ድጋፍ ማኅበራት ሰሞኑን መግለጫ አውጥተው ነበር።
የማኅበራቱ መግለጫ የሚጀምረው ኢትዮጵያ በውጭ ወረራ አደጋ ላይ እንደሆነች በማመላከት ነበርና ይህንን ሃረግ እንዲያራሩ ከመግለጫው አርቃቂዎች አንዱ የሆኑትን በደቡብ አፍሪካ ዊትዋተርስትራንድ ዩኒቨርሲቲና በአሜሪካው ዴንበር ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩትን ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽን አነጋግረን ነበር።
ከፕሮፌሰር ሰዒድ ሳዲቅ ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ ምልልስና ከፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ በአጭሩ ተወስዶ የተቀናበረው ዘገባ ከዚህ ጋር ተያይዟል፣ ያዳምጡት።
Your browser doesn’t support HTML5