በፌደራል ደረጃ እንዲዳኙ የተመረጡና የወንጀል ክስ ይቅረብ ወይስ አይቅረብ የሚለውን ብይን የሚሰጡ ከሕዝብ የተውጣጡ ዳኞች “የ2020ቱን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ለመቀልበስ ጥረት አድርገዋል” በሚል በሕግ ተጠያቂ ይሆኑ ዘንድ ጥያቄ በቀረበባቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን እና ሌሎች 18 ሰዎችን መክሰስ ተከትሎ፣ የዲሞክራቲክ ፓርቲው መሪዎች፣ ብይኑ ‘ማንም ከህግ በላይ እንዳልሆነ ያሳየ ነው’ ሲሉ የሪፐብሊካን ፓርቲው አንጋፋ አባላት በበኩላቸው ‘ለፖለቲካ ዓላማ ሲባል በ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪ ላይ የተፈጸመ ድርጊት ነው’ ሲሉ ይሞግታሉ።
በእንደራሴዎች ምክር ቤት የብዙኃኑ መሪ ቸክ ሹመር እና በምክር ቤቱ የዲሞክራቶች መሪ ሃኪም ጀፈሪስ በጋራ በሰጡት መግለጫ፡ የትላንቱ ክስ እና ከዚያ ቀደም ብሎ የቀረቡት ሶስት ክሶች፡ "የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ተደጋጋሚ ወንጀሎች" ያሳያሉ ብለዋል።
ሹመር እና ጀፈሪስ አክለውም፣ "በፉልተን አውራጃ አቃቤ ሕግ እና በሌሎች የግዛት እና የፌደራል አቃብያነ ኅጎች የተወሰዱት እርምጃዎች አሜሪካ ውስጥ ‘ፕሬዝደንቱን ጨምሮ ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይደለም’ የሚለውን የጋራ እምነትን በድጋሚ ያረጋግጣሉ" ብለዋል።
ከሪፐብሊካን ወገን የሆኑት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ኬቨን ማካርቲ ደግሞ ቀድሞ ‘ትዊተር’ ይባል በነበረው እና በዛሬው ‘X’ የማሕበራዊ ትስስር መድረክ ላይ ባሰፈሩት አስተያየት፡ “ፕሬዝደንት ጆ ባይደን “በ2024ቱ ምርጫ ጣልቃ ለመግባት፣ የመንግስትን ኃይል ዋናውን የፖለቲካ ተቀናቃኛቸውን ለማጥቂያነት ተጠቀሙበት” ብለዋል። የፉልተን አውራጃዋን አቃቤ ሕግ ፋኒ ዊሊስ’ንም "ፕሬዝደንት ትራምፕን ለማጥቃት እና የገዛ ፖለቲካ ስልጣናቸውን ለማጎልበት የሚረዳ አቅም ለመሰብሰብ አዋሉት" ሲሉ ወንጅለዋል።
የምርጫ ክልላቸው ጉዳዩ የተነሳበትን የፉልተን አውራጃን የሚጨምረው ዲሞክራቷ የምክር ቤት ተወካይ ኒኬማ ዊሊያምስ በበኩላቸው “ትራምፕ በ2020ቱ ፍትሃዊ ምርጫ የገጠማቸውን ሽንፈት መቀበል ባለመፍቀዳቸው ነው በጆርጂያ ግዛት ውስጥ ያለውን መራጭ ድምጽ ለመንጠቅ የሞከሩት” ሲሉ ተችተዋል።
ሌሎችም በርካታ አንጋፋ የፖለቲካ ሰዎች በየፊናቸው በድጋፍ እና በተቃውሞ ክሱን አስመልክቶ የየበኩላቸውን አስተያየት ሰንዝረዋል።