የጆርጂያ የምርጫ ውጤት ተቃውሞ ገጠመው

የጆርጂያ ፕሬዝደንት ሳሎሜ ዙራቢችቪሊ

በጆርጂያ በሳምንቱ መጨረሻ በተደረገው የፓርላማ ምርጫ ገዢው ፓርቲ እንዳሸነፈ መታወጁን ተከትሎ፣ በምርጫው ውጤት ላይ የሚደረገውን ተቃውሞ የምዕራቡ ዓለም እንዲደግፍ የሃገሪቱ ፕሬዝደንት ጥሪ አድርገዋል።

የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉ ያስታወቁት ፕሬዝደንት ሳሎሜ ዙራቢችቪሊ ሃገሪቱ የአውሮፓ ኅብረትን ለመቀላቀል በማቀዷ የሩሲያ ጫና ደርሶባታል ብለዋል። የገዢው ፓርቲ ተቃዋሚ መሆናቸው የሚታወቀው ፕሬዝደንት ሳሎሜ ለአሶስዬትድ ፕረሥ እንዳሉት፣ የጆርጂያ መንግስት “ከሩሲያ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በመሥራት ላይ ነው።” መንግስት ምናልባትም ከሩሲያ የደህንነት ኃይሎች እገዛ ሳያገኝ እንዳልቀረም ፕሬዝደንቷ ተናግረዋል።

ጆርጂያውያን በመዲናዋ ቲቢሊሲ ዛሬ ምሽት ተቃውሞ እንዲያደርጉም ፕሬዝደንቷ ጥሪ አድርገዋል።

አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅበረት በቅዳሜው ምርጫ ውጤት ላይ ሙሉ ምርምረራ እንዲደረግ ጥሪ አድርገዋል።

‘ጆርጂያን ድሪም’ የተሰኘው ገዢ ፓርቲ 54.8 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸናፊ መሆኑን የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል።

ፓርቲው የተቋቋመው በሩሲያ ሃብት ባከበቱት ቢሊየነር ቢድዚና ኢቫኒሽቪሊ እንደሆነ እና ፓርቲው ከክሬምሊን ጋራ ተመሳሳይ የሆነ ሕግጋትን በማውጣት ባለፈው አንድ ዓመት የመናገርና ሌሎችንም ነፃነቶች በመገደብ ላይ መሆኑ ተነግሯል።