የሰብአዊ ርዳታ ወደ ጋዛ እንዳይገባ መከለከል በወንጀል ሊያስጠይቅ እንደሚችል፣ ዓለም አቀፉ የወንጀል ችሎት ዋና አቃቤ ሕግ አስጠነቀቁ።
“በጀኒቫ ስምምነት መሠረት፣ የርዳታ አቅርቦቶችን ማገድ እንደወንጀል የሚቆጠርና ፍርድ ቤቱም የሚመለከተው ጉዳይ ይሆናል” ሲሉ ዋና አቃቤ ሕጉ ካሪም ካን ካይሮ ላይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
በግብጽ እና ጋዛ መካከል የሚገኘውን መተላለፊያ የጎበኙት ዋና አቃቤ ሕጉ፣ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ አቅርቦቶችን የያዙ የጭነት መኪኖች ማለፍ ሳይችሉ ቀርተው ቆመው መመልከታቸውን ተናግረዋል።
አቅርቦቶቹ ካለ ተጨማሪ መዘግየት በጋዛ ለሚገኙ ሲቪሎች መድረስ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ራፋ፣ በከበባ ውስጥ ላለውና በሃማስ በሚተዳደረው የፍልስጤም ግዛት ርዳታ ለማድረስ ብቸኛው መተላለፊያ ነው።
የሐማስን ደንገተኛ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በፈጸመችው ድብደባ እስከ አሁን 8ሺሕ ሰዎች ተገድለዋል።
ከሳምንት በፊት ርዳታ እንዲገባ መፈቀዱን ተከትሎ፣ 177 የጭነት መኪኖች ገብተዋል።