የእስራኤል ጦር ኃይሎች በጋዛ ሰርጥ ከ30 በላይ ዒላማዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ጦሩ ሐሙስ እለት ሲያስታውቅ፣ የጋዛ ሆስፒታል ባለስልጣናት በበኩላቸው እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት በደቡባዊው የራፋ ከተማ የሚኖሩ ቢያንስ አምስት ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይሎች ዒላማ ካደረጓቸው ቦታዎች መካከል፣ የሐማስ መጋዘኖች እና በማዕከላዊ ጋዛ ታጣቂዎቹ ወደ እስራኤል ጦር ሮኬቶች የሚያስወነጭፉባቸው አካባቢዎች እንደሚገኙበት አስታውቀዋል።
ጦርነቱ በጋዛ የቀጠለው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዛድንት ጆ ባይደን፣ እስራኤል ለወታደራዊ ወጪ የምታውለውን 26.4 ቢሊየን ዶላር ያካተተውን የ95 ቢሊየን ዶላር እርዳታ ከፈረሙ ከአንድ ቀን በኃላ ነው። በጀቱ ለጋዛ ንፁሃን ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ የሚውል አንድ ቢሊየን ዶላርም ያካትታል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብዓዊ እርዳታ በማከፋፈል ረገድ ገንቢ ሚና ሊጫወት የሚችልበትን መንገድ ነድፏል ያሉት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር የጋዛ ከፍተኛ የሰብዓዊ እና የመልሶ ግንባታ አስተባባሪ ሲግሪድ ካግ፣ ነገር ግን፣ የባህርም ሆነ የአየር ማጓጓዣዎች በጭነት የሚገቡ እርዳታዎችን መተካት አይችሉም ሲሉ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ አቅርቦቶችን በብዛት ለማስገባት የመሬት ማጓጓዣዎች ተመራጭ መሆናቸውን ተናግረዋል።