የጋምቤላ ክልላዊ መስተዳደር ፕሬዚዳንት በሙስና መገምገማቸውን አስተባበሉ

“ግምገማውን የመራሁት እኔ ነኝ፤ የፈደራል ተወካዮች ታዛቢዎች ነበሩ”

የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መስተደደር ፕሬዚዳንትና የቀድሞ የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ኡመድ ኡባንግ ኦሉም በቅርቡ በጋምቤላን በተካሄደ ግምገማ “ሰለሙስናም ሆነ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ስለ 2003 ዓመተ ምህረቱ የአኝዋክ ብሔረሰብ አባላት ፍጅት የተነሣ የለም” ብለዋል።

“ግምገማው በክልሉ የልማት መርኃግብርና የአስተዳደር ጉዳዮች ላይ ያተኮረና የአምስቱን ዓመት የሥራ ክንውን የተመለከተ እንጂ ከሙስና ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ ስም ማጥፋት እንጂ ሙስና የኔ ገፀ-ባህሪ አይደለም” ብለዋል፤ ካራቱሪ ከተባለው የህንድ ኩባንያ በብዙ ሚሊዮን ብር የሚገመት ጉቦ እንደተቀበሉ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ቪላ እንዳላቸው፤ በወንድማቸውና ሌሎች ዘመዶች ስም በርከት ያለ በባንክ ተቀማጭ ገቢ እንዳላቸው፤ በግምገማው ላይ ተነሣ የተባለውን ክሥ አስተባብለዋል።

“ታዲያ ለምን ከፓርቲ ሊቀመንበርነት እንዲነሱ ተደረገ?” ለሚለው ጥያቄ ግን “ድርጅቱን የመምራት አቅሜ ሰለተዳከመ ነው” የሚል መልስ ሰጥተዋል።

ቀደም ብሎ በግምገማው ወቅት የክልሉ ፕሬዚደዳንት የ2003 ዓመተ ምህረቱ የአኝዋኮች ፍጅት መወንጀላቸውን፣ ፕሬዚዳንቱም “ግድያውን አልፈፀምኩም፤ ሆኖም የአኝዋኮችን ስም ዝርዝር ግድያውን ለፈጸሙ የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ሰጥቻለሁ፣ እኔ በፍጅቱ የምከሰስ ከሆነ ትዕዛዙን ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጭምር መጠየቅ አለባቸው” ማለታቸውን አንድ የጋምቤላ ነዋሪና የመንግሥት ሠራተኛ ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ገልፀው ነበር። አቶ ኡመድ ግን “ጥያቄውም አልተነሣም፤ እኔም ይህንን መልስ አልሰጠሁም” ሲሉ አስተባለዋል።

ሙሉውን ቃለ ምልልስ ያዳምጡ።